Grade 5 Environmental Science 45 PDF
Document Details
Uploaded by LustrousSavanna6540
Abiyot Primary School
Tags
Summary
This document is a chapter from a grade 5 environmental science textbook in Ethiopia. It covers various aspects of Ethiopian culture, such as traditions, languages, and historical sites, aiming to promote cultural understanding and appreciation.
Full Transcript
Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ ምዕራፍ አራት ማኅበራዊ አካባቢ የምዕራፉ የመማር ውጤቶች ተማሪዎች ይህንን ምዕራፍ ተምራችሁ ስታጠናቅቁ፡- የኢትዮጵያን የባህል ብዝኀነት ዋጋ ትሰጣላችሁ፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ የባህል ክዋኔዎችን ትለያላችሁ፡፡ በኢትዮጵያ የሚ...
Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ ምዕራፍ አራት ማኅበራዊ አካባቢ የምዕራፉ የመማር ውጤቶች ተማሪዎች ይህንን ምዕራፍ ተምራችሁ ስታጠናቅቁ፡- የኢትዮጵያን የባህል ብዝኀነት ዋጋ ትሰጣላችሁ፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ የባህል ክዋኔዎችን ትለያላችሁ፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ ዋና ዋና የቋንቋ ቤተሰቦችን ትዘረዝራላችሁ፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ ባህላዊ ቅርሶችን በመለየት ታብራራላችሀ፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ ባህላዊና ዘመናዊ ተቋማትን በመለየት አስፈላጊነታቸውን ትገልጻላችሁ፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ ዐበይት ምጣኔ ሀብታዊ ዘርፎችን ትለያላችሁ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የተለያዩ የግብርና ተግባራትንና እንቅስቃሴዎችን በመለየት ትገልጻላችሁ፡፡ በኢትዮጵያ ወደ ውጭ የሚላኩ ዐበይት የግብርና ውጤቶችን ትዘረዝራላችሁ፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችን ፋይዳ ትመረምራላችሁ፡፡ ቱሪዝም በኢትዮጵያ የሚኖረውን ፋይዳ ትመረምራላችሁ፡፡ በኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ዐበይት ምክንያቶችን ትገልጻላችሁ፡፡ 104 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ የምዕራፉ ይዘት 4.1 የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ 4.2 ዋና ዋና የቋንቋ ቤተሰቦች በኢትዮጵያ 4.3 ባህላዊ ቅርሶች በኢትዮጵያ 4.4 ባህላዊና ዘመናዊ ተቋማት 4.5 የባህል ብዝኀነትና የብዝኀ ሕይወት መሠረቱና ታሪኩ 4.6 ዓቢይት የምጣነ ሀብት ዘርፎች በኢትዮጵያ1 4.7 ግብርና በምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ላይ የሚኖረው ሚና በኢትዮጵያ 4.8 የኢንዱስትሪ ዓይነቶች በኢትዮጵያ 4.9 የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዓይነቶች በኢትዮጵያ 4.10 ቱሪዝም በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚኖረው ሚና በኢትዮጵያ 4.11 በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ዋና ዋና ጉዳዮች መግቢያ ተማሪዎች በአራተኛ ክፍል የአካባቢ ሳይንስ ትምህርታችሁ በከተማችሁ ስለየሚገኙ የተለያዩ ባህሎች፣ ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ የሚረዱ ባህላዊ ክዋኔዎች፣ ዋና ዋና ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴዎች፣ በተፈጥሮ ሀብት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚሳድሩ ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴዎችን ተምራችኋል፡፡ በዚህ ክፍል ደግም በኢትዮጵያ የባህል ብዝኀነት፣ በጣም የተለመዱ ባህላዊ ክዋኔዎች፣ የባህል ይዘቶችና ባህላዊ ቅርሶች፣ ዋና ዋና የቋንቋ ቤተሰቦች እና በኢትዮጵያ የተለያዩ የምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴዎችን ትማራላችሁ፡፡ 105 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ 4.1 የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ የንዑስ ርዕሱ አጥጋቢ የመማር ብቃት፡- ተማሪዎች ይህን ክፍለ ትምህርት ተምራችሁ ስታጠናቅቁ፡- የኢትዮጵያን የባህል ብዝኀነት ዋጋ ትሰጣለችሁ፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ የባህል ክዋኔዎችን ትለያላችሁ፡፡ ቁልፍ ቃላት ብዝኀነት ባህል ተግባር 4.1 የግል ሥራ ዓላማ፡- የተለያዩ ባህሎችን ማሳወቅ መመሪያ፡- ተማሪዎች የምታውቋቸውን ባህላዊ ክዋኔዎች በተግባር ለክፍል ጓደኞቻችሁ አሳዩ፡፡ የአንድ ማኀበረሰብ አመለካከት፣ እምነት፣ መጠቀሚያ ቁሳቁስ፣ በዓል አከባበር፣ አመጋገብ፣ አለባበስ፣ ዕደ ጥበብ እና የመሳሰሉት ባህል በመባል ይታወቃሉ፡፡ ባህል የአንድ ማኀበረስብ የማንነት መገለጫ እና የህልውና መሠረት ነው፡፡ ባህል ማኀበረሰቡ ራሱ የሚፈጥረው፣ የሚተገብረው፣ የሚከውነው፣ የሚያከብረው እና የሚገዛለት ትልቅ መስተጋብር ነው፡፡ ስለዚህ ባህል የሌለው ማኀበረሰብ ወይንም ባለቤት የሌለው ባህል አይኖርም፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያም ከሰማንያ በላይ የሚሆኑ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባለቤት ናት፡፡ ሁሉም የሀገራችን ብሔርብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የራሳቸው ባህልና ወግ አላቸው፡፡ ባህል እና ወግ ስንል የራሳቸው የሆነ አለባበስ፣ አመጋገብ፣ በዓል አከባበር፣ የለቅሶ ሥነሥርዓት፣ የሠርግ ሥነሥርዓት፣ ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች፣ ባህላዊ ጭፈራዎች የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ እነዚህ የሀገራችን ህዝቦች ክንዋኔዎች የባህል ብዝሃነትን ይገልፃሉ፡፡ የባህል ብዝሃነት በአንድ ሀገር የሚገኙ እና የሚተገበሩ የተለያዩ ባህሎች ህልውና የሚገለፁበት እና አንዳቸው ለሌላቸው ውበትና ድምቀት ሆነው የሚታዩበትና ትስስራቸው ጎልቶ የሚወጣበት መገለጫ ነው፡፡ 106 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ ሥዕል 4.1 ሀ የጥምቀት በዓል አከባበር ሥዕል 4.1 ለ. የአረፋ በዓል አከባበር ሥዕል 4.1 ሐ. የሃረር፣ የሲዳማ፣የቤኒሻንጉል፣ የአፋር ብሄረሰቦች 107 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ በጣም የተለመዱ ባህላዊ ክዋኔዎች በኢትዮጵያ በሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ የተለመዱ ባህላዊ ክዋኔዎች ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም መካከል አሸንዳ፣ ሻደይ፣ ሶለል፣ ቡሄ ጭፈራ፣ ጨምበላላ፣ የገና ጨዋታ፣ የለቅሶ ሥነሥርዓት፣ የሠርግ ሥነሥርዓት፣ በበዓላት የሚደረጉ የተለያዩ ጭፈራዎች የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ አሸንዳ፣ ሶለልና ሻደይ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የሚከወኑ ተመሳሳይ የበዓል አከባበር ናቸው፡፡ነገር ግን በሚከወኑበት አካባቢ የተለያየ ስያሜ አላቸው፡፡ አሸንዳ በትግራይ፣ ሻደይ በላሊበላና ሰቆጣ ሶለል በወልድያ ይከናወናሉ፡፡ የባህል ይዘቶች በኢትዮጵያ ባህል ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲወራረስ የመጣ ስርዓት ነው፡፡ባህል የአንድ ማኀበረስብ የማንነት መገለጫ ነው፡፡ ለምሳሌ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በእንግዳ አቀባበል ይደነቃል፡፡ ባህል በኢትዮጵያ በርካታ ይዘቶች አሉት፡፡ ከነዚህም መካከል አለባበስ፣ አመጋገብ፣ ቋንቋ፣ የለቅሶ ሥነ ሥርዓት፣ ባህላዊ ጭፈራ፣ የበዓላት አከባበር፣ ችግር መፍቻ ሥርአቶችን እና የመሳሰሉትን ያጠቃልላል፡፡ ለምሳሌ በመስቀል በዓል አከባበር ምክንያት በሰሜን እና በደቡብ የሀገራችን ክፍሎች በሚገኙ ሕዝቦች በተለያየ ደማቅ በህላዊ ሥርዓት ይከወናል፡፡ በዓሉን ለማክበር የደመራ ችቦ የማብራት፣ የተለያዩ ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች ማዘጋጀት፣ ቤተሰብ ከቤተሰብ፣ ዘመድ ከዘመድ መገናኘት፣ አብሮ መብላት መጠጣትና በጋራ መጫወት በስፋት ይስተዋላል፡፡ ለበዓሉ አከባበር የተለያዩ አልባሳት በመልበስ ባህላዊ ጭፈራዎች ይታያሉ፡፡ በፍቼ ጨምበላላና በጊፋታ በዓልም በተመሳሳይ የተለያዩ ገፅታ ያላቸው ይዘቶች ይንፀባረቃሉ፡፡ በሌላ በኩል በሠርግና በለቅሶ ሥነ ሥርዓት ላይም የሚታዩት የአለባበስ፣ የአመጋገብና የእርስ በርስ ግንኙነቶች በሀገራችን ባህል ውስጥ በጉልህ የሚታዩ የባህል ይዘቶች ናቸው፡፡ 108 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ መልመጃ 4.1 በ ‹‹ሀ›› ሥር ተዘረዘሩትን ባህላዊ ክዋኔዎች በ ‹‹ለ›› ሥር ከተዘረሩት የክዋኔ አካባቢዎች ጋር አዛምዱ፡፡ “ሀ” “ለ” 1. አሸንዳ ሀ. ወልድያ 2. ጨምበላላ ለ. ወላይታ 3. ጊፋታ ሐ. ትግራይ 4. ሻደይ መ. ላሊበላና ሰቆጣ 5. ሶለል ሠ. ሲዳማ ለሚከተሉት ጥያቄዎች አጭር መልስ ስጡ 1. የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ እንዴት ይገለፃል? 2. በኢትዮጵያ ከሚገኙ ባህላዊ ክዋኔዎች ውስጥ የምታውቁትን መርጣችሁ ባህሉን የሚገልፅ አጭር ፅሁፍ ፅፋችሁ ለመምህራችሁ አቅርቡ፡፡ 4.2 ዋና ዋና የቋንቋ ቤተሰቦች በኢትዮጵያ የንዑስ ርዕሱ አጥጋቢ የመማር ብቃት፡- ተማሪዎች ይህን ትምህርት ተምራችሁ ስታጠናቅቁ ፡- በኢትዮጵያ የሚገኙ ዋና ዋና የቋንቋ ቤተሰቦችን ትዘረዝራላችሁ፡፡ ቁልፍ ቃላት ሴም ናይሎ ሰሐራዊ ኦማዊ ኩሽ የማነቃቂያ ጥያቄ ባህል እና ቋንቋ ያላቸውን ግንኙነት ግለጹ፡፡ ባህል የአንድ ኀብረተሰብ የአኗኗር ዘይቤ ነው፡፡ ባህል ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲወራረስ የመጣ የቋንቋ፣ የአለባበስ፣ የአመጋገብ፣ እምነቶችን፣ ዕደጥበባትን፣በዓላትን፣ 109 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ እና የምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴዎችን ያካትታል፡፡ ስለዚህ ቋንቋ የአንድ ሕዝብ ባህል መገለጫ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዋና ዋና የቋንቋ ቤተሰቦች ሀገራችን የተለያዩ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መኖርያ በመሆኗ ከሰማንያ በላይ ቋንቋዎች በላይ የሚነገሩባት ልሳነ ብዝኀነት የሚታይባት ሀገር ናት፡፡ በሀገራችን የሚነገሩ ቋንቋዎች በሁለት ዋና ዋና የቋንቋ ቤተሰቦች ይመደባሉ፡፡ እነርሱም፡- 1. አፍሮ እስያዊ እና 2. ናይሎ ሰሐራዊ በመባል ይታወቃሉ፡፡ የአፍሮ እስያዊ ዋና የቋንቋ ቤተሰብ በኩሽ፣ በሴም እና በኦሟዊ የቋንቋ ቤተሰቦች ይመደባል፡፡ በኢትዮጵያ የሚነገሩ ዋና የቋንቋ ቤተሰብ እና የቋንቋ ቤተሰቦች 1. የሴም ቋንቋ ምድብ 2. የኩሽ ቋንቋ ምድብ 3. የኦሟዊ የቋንቋ ምድብ 4. የናይሎ ሰሐራዊ ዋና የቋንቋ ምድብ ናቸው፡፡ በእያንዳንዱ ምድብ የተለያዩ ቋንቋዎች ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ሀ. የሴም ቋንቋ ምድብ ፡- አማርኛ፣ ስልጥኛ፣ ግዕዝ፣ አርጎብኛ፣ ጉራጊኛ፣ የሐረሪ፣ ትግርኛ እና ዛይ ቋንቋዎች ይገኛሉ፡፡ ለ. የኩሽ ቋንቋ ምድብ ፡- የአፋርኛ፣ የአዊኛ፣አገዊኛ፣ አላባኛ፣ ቡርጂኛ፣ ጌዴኦፋ፣ ሀድይሳ፣ ከምባትኛ፣ ኮንሶኛ፣ አፊ ሶማሌ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ሲዳሙ አፉ፣ የሶማሊኛ ቋንቋዎች ይመደባሉ፡፡ ሐ. የኦሟዊ ቋንቋ ምድብ፡- የቡርጂ፣የጋሞ፣ የሐመር፣ ካፊኖኖ፣ ኮንትኛ፣ የዳዋሮ፣ የባስኬቶ፣ የዶርዜ እና የወላይታቶ ቋንቋዎች ይገኛሉ፡፡ መ. የናይሎ ሰሐራዊ ዋና ቋንቋ ምድብ፡- የበርታ፣ የጉሙዝ፣ የአንፊሎ፣ የኑዌር እና የአሪ ቋንቋዎች ይገኛሉ፡፡ 110 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ የሴም ቋንቋ ተናጋሪዎች በአብዛኛው በሰሜን የሀገራችን ክፍል ይገኛሉ፡፡ የኩሽ ቋንቋ ተናጋሪዎች ደግሞ በማዕከላዊ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ይገኛሉ፡፡ የናይሎ ሰሐራዊ ቋንቋ ቤተሰብ ተናጋሪዎች ደግሞ በምዕራብ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የጠረፍ አካባቢዎች ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ በስፋት የሚነገሩ ቋንቋዎች የማነቃቂያ ጥያቄ በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት የሚነገሩ ቋንቋዎችን ጥቀሱ፡፡ በኢትዮጵያ ከሰማኒያ በላይ ቋንቋዎች ይነገራሉ፡፡ ከእነዚህ ቋንቋዎች ውስጥ አብዛኞቹ ቋንቋዎች ጥቂት ተናጋሪ ሲኖራቸው በተቃራኒው ጥቂት ቋንቋዎች ደግሞ በርካታ ተናጋሪዎች አሏቸው፡፡ ይህ የተናጋሪዎች ብዛት ቋንቋዎቹ በስፋት እንዲነገሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ለምሳሌ አፋን ኦሮሞ፣ አማርኛ፣ ሶማሊኛ፣ ትግርኛ፣ አፋርኛ፣ ሲዳሙ አፉ፣ እና ወላይታቶ በኢትዮጵያ በስፋት ከሚነገሩ ቋንቋዎች መካከል ሊመደቡ የሚችሉ ናቸው:: በተመሳሳይ ሌሎች ቋንቋዎችም ይኖራሉ፡፡ የቡድንውይይት 4.1 ዓላማ -የኢትዮጵያን ዋና ዋና የቋንቋ ቤተሰቦችን በመዘርዘር የሚነገሩባቸውን አካባቢዎች መለየት ¾ የኢትዮጵያን ዋና ዋና የቋንቋ ቤተሰቦችን በመዘርዘር የሚነገሩባቸውን አካባቢዎች ለክፍል ጓደኞቻችሁ አቅርቡ፡፡ 111 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ መልመጃ 4.2 የሚከተሉትን ጥያቄዎች በተሰጣችሁ ባዶ ቦታ ላይ መልሱን ጻፉ፡፡ 1. የኢትዮጵያ ዋና ዋና የቋንቋ ቤተሰቦች _______________ እና ______________ ናቸው፡፡ 2. በአፍሮ ኤስያዊ ዋና የቋንቋ ቤተሰብ ስር የሚመደቡ የቋንቋ ቤተሰቦች ________________፣ _________________እና _________________ ናቸው ፡፡ 3. በሰሜን ኢትዮጵያ የሚነገረው የቋንቋ ቤተሰብ ________ ነው፡፡ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ከሚገኙበት የቋንቋ ቤተሰብ ምድብ ጋር በማዛመድ በተሰጣችሁ ባዶ ቦታ ላይ ይህን () ምልክት አስፍሩ፡፡ ተቁ. ቋንቋዎች የኩሽ ቋንቋ የኦሟዊ ቋንቋ የሴም ቋንቋ 1 ኮንታ 2 ዳዋሮ 3 ባስኬቶ 4 ዶርዜ 5 ጌዴኦፋ 6 ሀድይሳ 7 ከምባታ 8 ኮንሶ 9 ጉራጌ 10 አደሬ 11 ትግርኛ 112 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ 4.3 ባህላዊ ቅርሶች በኢትዮጵያ አጥጋቢ የመማር ብቃት ተማሪዎች ይህን የትምህርት ይዘት ተምራችሁ ስታጠናቅቁ፡- በኢትዮጵያ የሚገኙ ባህላዊ ቅርሶችን በመለየት ታብራራላችሁ፡፡ ቁልፍ ቃላት ባህላዊ ቅርስ የሚዳሰሱ ቅርሶች የማይዳሰሱ ቅርሶች የቡድን ውይይት 4.2 ዓላማ፡- የኢትዮጵያን ባህላዊ ቅርሶች ማስተዋወቅ የመወያያ ጥያቄዎች 1. ቅርስ ምንድን ነው? 2. በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ባህላዊ ቅርሶችን በመዘርዘር የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ በማለት መድቡ፡፡ ኢትዮጵያ የበርካታ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ባለቤት ናት፡፡ ቅርስ የጥንት ሰዎች የዕውቀትና የስልጣኔ ደረጃ መገለጫ ቁስ ወይም በተፈጥሮ የተገኘ አእምሮንና መንፈስን የሚያድስ ውድ ሃብት ነው፡፡ ቅርስ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ተብሎ በሁለት ይከፈላል:: በተጨማሪም ቅርስ የሚታይና የሚዳሰስ (ቁሳዊ ቅርስ)ና የማይታይና የማይዳሰስ (ረቂቅ ቅርስ) ተበሎ ይከፈላል፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ባህሎችን የመጠበቅና የማስተዋወቅ ዘዴዎች የቡድን ውይይት 4.3 የመወያያ ጥያቄ፣- ኢትዮጵያውያን ባህሎቻቸውን ለማስተዋወቅ የሚጠቀሙባቸውን ዘዴዎችን ዘርዝሩ ኢትዮጵያውያን ባህሎቻቸውን ለመጠበቅ ምን ምን ዘዴዎችን ይጠቀማሉ? 113 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ ባህል ሲተዋወቅ ባህሉን የሚያከብር ህዝብ፣ ባህሉ የሚከበርበት ቦታ፣ በዓሉ የሚታይበት ቀንና ባህሉ የሚገለጽበት አልባሳትና እንቅስቃሴዎች በግልፅ ይታወቃሉ:: በዚህ መሠረት ብሔር ብሔረሰቦች ባህላቸውን የሚጠብቁበትና የሚያስተዋውቁበት ክዋኔ ያሳያሉ፡፡ ባህላዊ ክዋኔዎቹም በሚከተሉት መንገዶች ይተዋወቃሉ፡፡ የባህል አከባበር ሥርዓት በማዘጋጀት፣ የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ሥራዎችን በመሥራት፣ የተለያዩ የዕደ-ጥበብ ሥራዎችን በመስራት መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም፣ ባህላዊ እንቅስቃሴዎችን በማዘጋጀት፣ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማብዛት ባህላዊ አልባሳትን በመስራትና በመልበስ ባህላቸውን ያስተዋውቃሉ፡፡ የሚዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች በኢትዮጵያ የአንድ ቅርስ ቅርጽ፣ መጠን፣ ዓይነትና ሥሪት የሚታወቅ ወይም እነዚህን በመጠቀም ማሳወቅ የሚችል ከሆነ የሚዳሰስ ቅርስ ይባላል፡፡ ሐውልቶች፣ የሕንጻ አሠራሮች፣ ትክልድንጋዮች፣ ጥንታዊ ሳንቲሞች፣ ጥንታዊ የድንንጋይ ላይ ጽሑፎች፣ የብራና ጽሑፎች፣ የተለያዩ ሥዕላዊ መግለጫዎች፣ ጌጣጌጦችና ዋሻዎች የሚዳሳሱ ቅርሶች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ቁሳዊ ቅርሶች መካከል የአክሱም ሐውልቶች፣ የጎንደር አብያተ መንግሥታት፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን፣ የሐረር ግንብ፣ የጥያ ትክል ድንጋዮች፣ የታችኛው የአዋሽ ሸለቆ፣ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ፣ የስሜን ተራራ ብሔራዊ ፓርክ፣ የኮንሶ እርከንና መልክዓ ምድር በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ሀ. የአክሱም ሐውልት አክሱም የመንግስት፣ ምጣኔ ሀብትና የሃይማኖት ማዕከል ነበረች፡፡ የጥንት አክሱማውያን ያለዘመናዊ መሣሪያያ ያቆሟቸው ግዙፍ ሐውልቶችና በሐውልቶቹ ላይ የሚታዩ ንድፎች እጅግ አስደናቂ ናቸው፡፡ በርካታ ትናንሽ ሐውልቶች ይገኛሉ፡፡ አንደኛው ሐውልት በኢጣሊያ ወረራ ወቅት ተዘርፎ በሮም አደባባይ ቁሞ ነበር፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያውያንና በሌሎች ወዳጅ ሀገሮች ያልተቋረጠ ጥያቄ ወደነበረበት ተመልሷል፡፡ በጣም ትልቁ ሐውልት ወድቆ ይገኛል፡፡ ሁለተኛው ከኢጣሊያ የተመለሰው ሲሆን ሦስተኛው አሁንም ቁሞ የሚገኘው ነው፡፡ 114 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ ሥዕል:4.4 የአክሱም ሐውልት ለ. የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያንናት ላሊበላ በሰሜን ወሎ ዞን የሚገኝ የጥንታዊ መንግስት፣ የምጣኔ ሀብትና የሃይማኖት ማዕከል ነበር፡፡ ይህ ከተማ ጥንት ሮሐ ወይም አዳፋ በመባል ይታወቅ ነበር፡፡ ዛሬ የሚጠራበትን ሥያሜ ያገኘው ከቋጥኝ አለቶች አሥራ አንድ አብያተ ክርስቲያናት በማነጽ ከሚታወቀው ገናናው ንጉሥ ዐፄ ላሊበላ የነገሱበት ዘመን ስም ነው፡፡ ዐፄ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናቱን ያሠሩት በኢትዮጵያ ዳግማዊ ኢየሩሳሌምን ለመገንባት ነው፡፡ ዛሬም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስቲያኖች ቦታውን እንደ ኢየሩሳሌም ይቆጥሩታል:: እንዲሁም እንደ ኢየሩሳሌም ደብረ ዘይት፣ ደብረ ታቦርና የዮርዳኖስ ወንዝ ስያሜ የተሰጣቸው ቦታዎች በዙሪያው ይገኛሉ፡፡ የላሊበላ 11 ውቅር አብያተ ክርስቲያንናት 1. ቤተ ማርያም 7. ቤተ አባ ሊባኖስ 2. ቤተ መድኃኔዓለም 8. ቤተ ገብርኤል 3. ቤተ ጊዮርጊስ 9. ቤተ መርቆሪዎስ 4. ቤተ ደናግል 10. ቤተ-አማኑኤል 5. ቤተ መስቀል 11. ቤተ ጎልጎታ 6. ቤተ ሚካኤል 115 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ ስዕል 4.5 የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በከፊል ሐ. የሐረር (የጀጎል) ግንብ የሐረር ግንብ በአሚር ኑር ኢብን ሙጀሂድ አማካኝነት በ1551 እ.ኤ.አ(እንደ ኤሮፓውያን አቆጣጥር) የከተማውን ሕዝብ ከጥቃት ለመከላከል የተገነባ ነው፡፡ ግንቡ በተለያዩ አቅጣቻዎች የሚገኙ አምስት በሮች አሉት፡፡ እነርሱም፦ ኤረር በር፣ ፋላና በር፣ ሸዋ በር፣ ቡዳ በርና ሳንጋ በር ናቸው፡፡ ስድስተኛው በር የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ልጅና አልጋ ወራሽ በልዑል ራስ መኮንን የነገሱበት ዘመን የተጨመረ ሲሆን ዱከ በር ይባላል፡፡ በዚህ በር ላይ የሐረር 75ኛ ገዥ የነበሩት አሚር አብዱላሂ የነገሱበት ምስል ያለበት ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ዋና መግቢያ በር በመሆን ያገለግላል፡፡ ይህ ግንብ በመካከለኛው የታሪክ ዘመን በሀገራችን የነበረውን የኪነ-ሕንጻ ጥበብ የሚያሳይ ነው፡፡ ሥዕል 4.6 የሐረር ግንብ 116 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ መ. የጎንደር አብያተ መንግሥታት የጎንደር አብያተ መንግሥታት በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር ከተማ የሚገኙ ሲሆን በአብዛኛው የፋሲል ግንብ በመባል ይጠራሉ፡፡ ይህንም ስያሜ ያገኙት በጣም አስደናቂ የሆነውን ግንብ ካሰሩት ዐፄ ፋሲለደስ የነገሱበት ስም ነው፡፡ በአንድ ግቢ ውስጥ ስድስት ግንቦች ይገኛሉ፤እነዚህም ስድስት ነገስታት በንግሥና ዘመናቸው ያሰሯቸው ናቸው:: እነርሱም የዐፄ ፋሲለደስ፣ የአፄ እያሱ፣ የዐፄ በካፋ፣ የዐፄ ዳዊት፣ የዐፄ ዮሐንስና የእቴጌ ምንትዋብ አብያተ መንግስታት ናቸው፡፡ በ17ኛው ክፍለ ዘመን የታነጹና የኢትዮጵውያንን የኪነ-ጥበብ ችሎታና የሥነ-ሕንጻ ሥልጣኔ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ሥዕል4.7 የጎንደር አብያተ መንግሥታት ሠ. የሰሜን ተራራ ብሔራዊ ፓርክ የሰሜን ተራራ ብሔራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ የዱር እንስሳትና አእዋፍ የሚኖሩበት ተፈጥሮአዊ ቅርስ ነው፡፡ በፓርኩ ዝርያቸው ሊጠፉ የተቃረቡና በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ዋልያ፣ ጭላዳ ዝንጀሮና ቀይ ቀበሮ ይገኙበታል፡፡ ሥዕል 4.8 የስሜን ተራራ ብሔራዊ ፓርክ 117 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ ረ. የጥያ ትክል ድንጋዮች የጥያ ትክል ድንጋዮች በደቡብ ክልል በጉራጌ ዞን በሶዶ ወረዳ የሚገኙ ከ36 በላይ ትክል ድንጋዮች ናቸው፡፡ ትልቁ ትክል ድንጋይ 5 ሜትር ከፍታ አለው፡፡ በትክል ድንጋዮቹ ላይ የተለያዩ ቅርጽና ሥዕሎች ይታያሉ:: የጥያ ትክል ድንጋይ የቀደምት ኢትዮጵያውያን የፈጠራ ውጤትና የእውቀት መገለጫ ነው፡፡ ሥዕል 4.9 የጥያ ትክል ድንጋዮች ሰ. የኮንሶ መልክዓ ምድር ኮንሶ በደቡብ ኢትዮጵያ ይገኛል፡፡ ድሮም በዚህ ቦታ ይኖር የነበረው ህዝብ አፈሩ በዝናብ እንዳይሸረሸር ለመከላከልና የተፈጥሮ ሃብትን ለመጠበቅ የድንጋይ እርከን በመስራት ይታወቃል፡፡ ይህ የድንጋይ እርከን ለመልክዓ ምድሩ ውበትን አጎናጽፎታል፡፡ ሥዕል 4.10 የኮንሶ መልክዓ ምድር 118 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ ቀ. የታችኛው የአዋሽ ወንዝ ሸለቆ በአፍሪካ አህጉር ዋናው የቅሪተ አካል መገኛ ስፍራ ነው፡፡ በሀገራችን ኢትዮዺያ በአፋር ክልል የታችኛው የአዋሽ ወንዝ ሸለቆ በጥንታዊ ቅሪት አካል የበለፀገ ቦታ ነው፡፡ በ1974 ዓ.ም 3.2 ሚሊዮን እድሜ ያስቆጠረችው ሉሲ የተገኘችበት ስፍራ ነው፡፡ 4.4 ሚሊዮን አመታት ያስቆጠረችው አርዲም በዚህ ቦታ ተገኝታለች፡፡ ቦታው ሀገራችን የሰው ዘር መገኛ እንደሆነች ያሳወቀና ስለ ታሪክ፣ ስለ ሰው ዘር የነበረውን ሀሳብ የቀየረ ስፍራ ነው፡፡ 3.6 ሚሊዮን አመታት ያስቆጠረችው የሶስት አመት ህፃንዋ ሰላምም በዚሁ ቦታ ተገኝታለች፡፡ ሸለቆው የሰው ዘርና የአትክልት ቅሪት በዙሪያው የተገኘበት ነው፡፡ ሥዕል 4.11 የታችኛው የአዋሽ ወንዝ ሸለቆ በ. የታችኛው የኦሞ ወንዝ ሸለቆ በታችኛው የኦሞ ወንዝ ሸለቆ በተደረገው የከርሰ ምድር ቁፋሮ ጥንታዊ ቅሪት አካላት ስለተገኙበት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል፡፡ 119 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ ሥዕል4.12 የታችኛው የኦሞ ወንዝ ሸለቆ በከፊል የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች በኢትዮጵያ የማይዳሰስ ቅርስ (ረቂቅ ቅርስ) በዓይን የማይታይና የማይጨበጥ ነገር ግን በድምጽ ወይም በአካላዊ እንቅስቃሴ የሚገለፅ አንድ ህዝብ በቅብብሎሽ ወይም በትውፊት ያገኘው ሃብት ነው፡፡ እነዚህም ትውፊታዊ አበባሎች፣ ሥነ ቃሎች፣ ጭፈራዎች፣ ቀረርቶዎችና ሽለላዎች፣ እንጉርጉሮዎች፣ የበዓል አከባበር ክንዋኔዎች ወዘተ ናቸው፡ ፡ ለምሳሌ የጥምቀት በዓል አከባበር፣ የመስቀል በዓል አከባብር፣ የኢሬቻ በዓል አከባበር፣ የፍቼ ጨምበለላ በዓል አከባበር፣ የቡሔ ጭፈራ፣ የአሸንድዬ፣ ሶለልና ሻደይ የመሳሰሉት የሀገራችን የማይዳሰሱ ቅርሶች ናቸው፡፡ የቡድን ውይይት 4.4 መመሪያ፡- አምስት አምስት ሆናችሁ በመወያየት የደረሳችሁበትን ድምዳሜ አንድ ተማሪ በመወከል ለክፍል ጓደኞቻችሁ አቅርቡ፡፡ የኢትዮጵያ ቅርሶች በአለም ቅርስነት መመዝገብ የሚያሰገኘው ጠቀሜታ ምንድን ነው? በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ የኢትዮጵያ ባህላዊ ቅርሶች አንድ ቁስ ወይም ክዋኔ በዓለም ቅርስነት ለመመዝገብ ከሚከተሉት መስፈርቶች አንዱን ማሟላት ይኖርበታል፡፡ 1. ከፍተኛ የፈጠራ ስራ የታየበት 2. በሥነ-ህንጻው፣ በአሰራሩና በንድፉ ዘመናትን የተሻገሩ ዕሴቶችን ማንጸባረቅ 3. የተረሳ ወይም የጠፋ ባህላዊ ትውፊትን ወይንም ሥልጣኔን ማሳየት 120 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ 4. ልዩ ተፈጥሮአዊ ውበትና ሥነ ውበታዊ ጠቀሜታ መያዝ 5. መልክአ ምድራዊ ለውጦችን ማሳየት 6. ሥነ ህይወታዊ ለውጦችን የሚያሳይ፣ ብዝኃ ህይወትን የሚገልጽ፣ በተፈጥሮ አካባቢ ለመጥፋት የተቃረቡ ዝርያዎች የሚገኙበት መሆን ይኖርበታል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ቁሳዊና መንፈሳዊ ቅርሶች አሏት፡፡ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ቁሳዊ ቅርሶች ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ 11 ቁሳዊ ቅርሶች አሏት፡፡ አነርሱም፡- 1. የአክሱም ሐውልት 2. የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት 3. የጎንደር አብያተ መንግስታት 4. የሐረር ግንብ 5. የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ 6. የጥያ ትክል ድንጋይ 7. የኮንሶ መልክዓ ምድር 8. የታችኛው የአዋሽ ወንዝ ሸለቆ 9. የታችኛው የኦሞ ወንዝ ሸለቆ ናቸው:: በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ የኢትዮጵያ መንፈሳዊ ቅርሶች 1. የጥምቀት በዓል 2. የመስቀል በዓል 3. ፍቼ ጨምበለላ 4. የገዳ ሥርዓት እና 5. ኢሬቻ ናቸው:: 121 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ መልመጃ 4.3 1. በሰንጠረዡ ውስጥ የተጠቀሱ ቅርሶችን በምድባቸው መሰረት()ይህን ምልክት በመጠቀም አሳዩ፡፡ የሚዳሰስ የማይዳሰስ በዓለም በዓለም ቅርስነት ቅርስነት ቅርስ የተመዘገበ ያልተመዘገበ የቡሄ ጭፈራ የጥያ ትክል ድንጋይ ፍቼ ጨምበለላ የመስቀል በዓል አከባበር የአክሱም ሐውልት ኢሬቻ የአገው የፈረስ ጉግስ ጊፋታ(የወላይታ) ባህላዊ ቅርሶችን ለመንከባከብና ለመጠበቅ የመንግሥት ተግባርና ኃላፊነት በኢትዮጵያ ባህላዊ ቅርሶችን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ሥልጣን የተሰጠው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሚከተሉት ተግባርና ሃላፊነቶች አሉት፡፡ ቅርሶችንና ባህሎችን ለመጠቀምና ለመጠበቅ የሚያስችል ፖሊሲዎችንና መመሪያዎችን ማውጣትና ማስፈፀም ያረጁ ቅርሶችን ይዘታቸውን ሳይለቁ የመጠገን፣ ለቁሳዊ ቅርሶች ጥበቃ ማድረግ፣ መንከባከብ ለቱሪስት ምቹ እንዲሆኑ ማድረግ ሰዎች ባህሎቻቸውን እንዲያሰተዋውቁ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ባህሎችንና ቅርሶችን ለዓለም ማስተዋወቅ፤ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ ለተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) ማሳወቅ፡፡ 122 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ 4.4 ባህላዊና ዘመናዊ ተቋማት አጥጋቢ የመማር ብቃት ተማሪዎች ይህን የትምህርት ይዘት ተምራችሁ ስታጠናቅቁ፡- በኢትዮጵያ የሚገኙ ባህላዊና ዘመናዊ ተቋማትን ትለያላችሁ፡፡ ባህላዊና ዘመናዊ ተቋማትን አስፈላጊነታቸውን ትገልጻላችሁ፡፡ ቁልፍ ቃላት ባህላዊ ተቋማት ዘመናዊ ተቋማት የማነቃቂያ ጥያቄ ባህላዊ ተቋማት ማለት ምን ማለት ነው? የባህል ተቋማት፡ ባህላዊ፣ ሳይንሳዊ እና አካባቢያዊ እውቀትን በመጠበቅ፣ በመተርጎም እና በማሰራጨት እንዲሁም ተጓዳኝ የባህል፣ የታሪክ፣ የሳይንስ እና የአካባቢ ገጽታዎችን ዜጎችን ለማሳወቅ እና ለማስተማር የታቀዱ ተግባሮችን ለማስተዋወቅ እውቅና የተሰጣቸው ተልእኮ ያላቸው ተቋማት ናቸው። እነዚህ ተቋማት በማኅበረሰቡ የተቋቋሙና በማህበረሰቡ ውስጥ ጉልህ ተግባራትን በማከናወን የሰዎች የጋራ እንቅስቃሴ እና የሰዎች ግንኙነቶች ለማጠናከር የተደራጁ ተቋማት ናቸው፡፡ ሰዎች በኃዘንና በደስታ ጊዜ በጋራ የሚያከናውኑት ጠቃሚ ማህበራዊ ዕሴቶችም በተቋሙ ውስጥ ይካተታሉ፡፡ ለምሳሌ ዕድር፣ ዕቁብና የመሳሰሉት ባህላዊ ተቋማት ናቸው፡፡ የቡድን ውይይት 4.5 የተለያዩ ባህላዊ ተቋማትን በመዘርዘር የሚሰጡትን ጥቅሞች ተወያይታችሁ ለክፍል ጓደኞቻችሁና ለመምህራችሁ አበራሩላቸው፡፡ ዕድር፡- ሰዎች በበጎ ፈቃደኝነት የሚመሠርቱት ማኅበራዊ ተቋም ነው፡፡ በኃዘን ጊዜ ኃዘንተኛውን ማጽናናት፣ የቀብር ሥርዓት ማስፈጸምና እንግዳ ተቀብሎ መሸኘት የዕድር አባላት የሚያከናውኑት ተግባር ነው፡፡ የዕድር አባላት ለሁሉም በእኩል ደረጃ ያለ ምንም ልዩነት በኃዘን ጊዜ ተገቢውን ትብብር ያደርጋሉ፡፡ ከመካከላቸው የተቸገረ ሲኖርም ይረዳዳሉ፡፡ ይህ ባህላዊ ተቋም የተለያዩ ገጽታዎች ቢኖሩትም ለረጅም 123 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ ዘመናት የቆየ የመረዳጃ ተቋም ነው፡፡ ዕድር በጾታ የወንድና የሴት፣ የአካባቢና የሀገር እንዲሁም፣ የሰፈርና የሀገር ዕድር ተብሎ ሊመሠረት ይችላል፡፡ እያንዳንዱ ዕድር ሰብሳቢ፣ ጸሐፊ፣ ገንዘብ ያዥና አባላት አሉት፡፡ በተጨማሪም የዕድሩ መተዳደሪያ ደንብ በሚያዘው መሠረት አባላቱ እርስበርስ የሚረዳዱበት ባህላዊ ተቋም ነው፡፡ ዕድርተኞች እንግዳ መቀበያ ድንኳን ይተክላሉ፣ ምግብ ያዘጋጃሉ፡፡ ስዕል፡ 4.13 የዕድር አባላት ዕቁብ:- ደግሞ ሌላው የአካባቢያችን ሰዎች የሚረዳዱበት ማኅበራዊ ተቋም ነው፡፡ ሰዎች ከገቢያቸው ቆጥበው ገንዘብ በማዋጣት በየጊዜው ለአባላቸው በእጣ ወይንም በትብብር መልክ ገንዘብ የሚያበድሩበትና የሚበደሩበት ማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ነው፡፡ የዕቁብ ገንዘብ ለተፈለገው አገልግሎት የሚቆጥቡበት እሴት ነው፡፡ ዕቁብ የራሱ ሰብሳቢ፣ ጸሐፊና አባላት ሲኖሩት የአገልግሎት ዘመኑም በወራት ወይም በዓመታት ሊገደብ ወይም በየጊዜው የሚታደስ ሊሆን ይችላል፡፡ ዕቁብ የመቋቋሚያ ደንብና የአሠራር ሥርዓት ያለው ማኅበራዊ ተቋም ነው፡፡ ባህላዊ የሕክምና ተቋማት የባህል ህክምና ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ህክምና ከተጀመረ ከመቶ ዓመት አይበልጥም፡፡ ከዚያ በፊት ሰዎች ሲታመሙ ህክምና የሚያገኙት በባህላዊ የህክምና ዘዴ ነበር፡፡ ባህላዊ ህክምናዎች በልምድ ብቻ የሚሠራባቸው መሆኑ ዕውቀቱ በተወሰኑ አካባቢዎችና ሰዎች ብቻ ተወስኖ እንዲቀር አድርጎታል፡፡ ባህላዊ መድኃኒትና ቅመማ፣ ምን ተቀላቅሎ ለምን ዓይነት በሽታ ፈውስ እንደሚሆን በአንዳንድ ሰዎች በሚሥጢራዊነት የተያዘ ቢሆንም በግዕዝ ቋንቋ የተጻፉ 124 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ የብራና መጽሐፍት ላይ ይገኛል፡፡ ነገር ግን የግዕዝ ቋንቋ ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ እየተዳካመ በመምጣቱና በቤተ ክህነት ብቻ መወሰኑ እነዚህ ጽሑፎች እንዳይነበቡና የያዙት ዕውቀት ጥቅም እንዳይሰጥ አድርጎታል፡፡ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ግን በኢትዮጵያ የብራና መጽሐፍት ላይ ያለውን ዕውቀት ለማግኘት የግዕዝ ቋንቋን እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድረስ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ የተለያዩ የዕፅዋት ቀንበጥ፣ ቅጠል፣ ቅርፊት፣ ሥር፣ ግንድ፣ የእንስሳት ተዋፆኦዎችና የተለያዩ ማዕድናት ለባህላዊ ህክምና ዋና ግብአቶች ናቸው፡፡ ጤና አዳም፣ ዝንጅብል፣ ዳማከሴ፣ ኮሶ፣ ሬት፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ሎሚ የመሳሰሉት አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በባህላዊ መንገድ ራሱን ለማከም ከሚጠቀምባቸው በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ጤና አዳም:- ቅጠሉም ሆነ ፍሬው ለጉንፋን፣ ለሆድ ህመም፣ ለመተንፈሻ ቧንቧ ችግር፣ ለቁርጥማትና ሌሎች ህመሞች ፈዋሽ መድኃኒት ነው፡፡ ነጭ ሽንኩርት:- ለጨጓራ፣ ለመተንፈሻ አካል ህመሞች ፈውስ፣ ደም በሰውነት ውስጥ እንዲዘዋወርና ምግብ በደምብ እንዲንሸራሸር ያደርጋል፡፡ ቀበርቾ:- ስሩን በመቀጥቀጥ ለድንገተኛ ህመም፣ ለውጋት ወዘተ ፈዋሽ መድሃኒት ነው፡፡ ኮሶ:- ፍሬውን ወይም ቅጠሉ ለኮሶ ትል በሽታ ፈዋሽ መድኃኒት ነው፡፡ እንቆቆ:- ፍሬው ለኮሶ ትል በሽታ ፈዋሽ መድኃኒት ነው፡፡ ብሳና:- ቅጠሉ ለወባ በሽታ መድኃኒትነት ያገለግላል፡፡ ሽፈራው:- ሽፈራው ከሚለው ስያሜ ባሻገር የጎመን ዛፍ ወይም የአፍሪካ ሞሪንጋ Moringa stenopetala) እስካሁን ድረስ በዓለም ዙሪያ የሽፈራው እያንዳንዱ ክፍል ሙሉ በሙሉ በተለያየ መልኩ ለመድሃኒትነት ይውላል። ለምሳሌ የደም ማነስና የጉበት ችግርን ማከም ይችላል። ሳማ:- ቅጠሉ ሥሩና ዘንግ መሳይ ቀጫጭን ግንዱ ለኩላሊት፣ የደም ስኳርን ለመቀነስ፣ ለምግብ መፍጫ የሰውነት ክፍሎችና ለመሳሰሉት በሽታዎች መድኃኒትነት ያገለግላል:: ዳማ ከሴ:- ቅጠሉን በመጭመቅና በማሽተት ወይም ቅጠሉን በውሃ አፍልቶ በመታጠብ ወይም በመጠጣት የምች መድኃኒት ሆኖ ያገለግላል፡፡ 125 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ ባህላዊ የውበት መጠበቂያ ተቋማት በሀገራችን የተለያዩ ባህላዊ የውበት መጠበቂያ ዘዴዎች አሉ፡፡ እነዚህ የውበት መጠበቂያ ዘዴዎች ውበትን አጉልተው ለማሳየትና ጤንነትን ለመጠበቅ ይጠቅማሉ፡፡ ለምሳሌ ቦለቅያ፣ የወይባ ጭስ፣ እርድ፣ ቀስል፣ እንሶስላ፣ ሂና እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ በርካታ ባህላዊ የውበት መጠበቂያ ዘዴዎች አሉ፡፡ ዘመናዊ የውበት መጠበቂያ ዘዴዎች በሀገራችን ከመጀመሩ በፊት ሰዎች ባህላዊ የውበት መጠበቂያ ዘዴዎችን ይጠቀሙ ነበር፡፡ እንሶስላ፡- የእጅና የእግር ውበትና ልስላሴ እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ ቦለቅያ፡- የተቆረጠ የወይባ እንጨትና ጭስ ነው፡፡ የወይባ ቅርፊት ሲፈላ ቢጫ ቀለም ያለው ሲሆን የምትታጠነው ሴት ቆዳ ቢጫ ቀለም ሲለብስ ጥራት ይኖረዋል፡፡ የወይባ ጭስን በተፈለገና በተመቸ ጊዜ መሞቅ የሚቻል ቢሆንም ጠዋት ወይም ማታ ተመራጭ ጊዜያት እንደሆኑ ይነገራል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ከሰዓት በኋላ የሚሞቅ ወይባ በተለይ ለወጣት ሙሽራ ሴቶች ውበትንና ጥራትን ያጎናፅፋል፡፡ የወይባ ዛፍ መሞቅ ለቆዳ ጥራትና መልካም ውበትን ለመላበስ፣ ሰውነት ጥሩ ጠረንና መዓዛ እንዲኖረው ያድርጋል፡፡ እንደ አጋም፣ እሬት፣ ምስርችና ጉመር የተባሉ የዛፍ ዓይነቶች ከወይባ ዛፍ ጋር አብሮ መሞቅ ለበርካታ በሽታዎች ለአብነትም ለሰውነት ቁርጥማት፣ እግርና ለአጠቃላይ ሰውነት መተሳሰር እንዲሁም ለወገብ በሽታና ድብርትን በመቅረፍ ረገድ ፈዋሽ ነው፡፡ ዘመናዊ ተቋማት የማነቃቂያ ጥያቄ ዘመናዊ ተቋም ማለት ምን ማለት ነው? ዘመናዊ ተቋማት- ሳይንሳዊና ቴክኖሎጂ ዕውቀትን በመጠቀም ዜጎችን ለማገልገል የተቋቋሙ ተቋማት ናቸው፡፡ 1.ባንክ፡- ለግለሰቦች ወይም ተቋማት ገንዘብ የማስቀመጥ እና የተቀመጠውን ገንዘብ ለሌሎች ተቋማት ወይም ግለ-ሰቦች የማበደር ተግባር የሚያከናውን የገንዘብ ተቋም ነው። ባንኮች ዋነኛ የምጣኔ ሀብት ዘርፍ ተዋናይ ናቸው። በዚህም ለማኅበራዊ ግብይት 126 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ መሠረት ናቸው። የባንኮች ዋነኛ ዓላማ ገንዘብ (ካፒታል) ያላቸውን ሰዎች ወይም ተቋማት ከሌላቸው ወይም ብድር ከሚፈልጉ አልያም ማደግን ከሚፈልጉ ተቋማት ጋር ማገናኘት ነው። ባንኮች በተቀማጭ መልክ ከግለሰቦች ወይንም ከድርጅቶች ያገኙትን ገንዘብ ለተበዳሪዎች ወለድ ጨምረው በማበደር ለትርፍ ይሠራሉ። በሀገራችን የንግድ ወይም የድርጅት ባንኮችን እና የኢንቨስትመንት ባንኮችን ጨምሮ በርካታ የተለያዩ ባንኮች ይገኛሉ። 2.መድን /ኢንሹራንስ/ መድን ማለት አስቀድሞ በሚደረግ አነስተኛ መዋጮ አባል ወይም ቤተሰቦች ችግር ሲያጋጥማቸው ለችግሮቻቸው ወጪዎች የሚሸፈኑበት መንገድ ነው፡፡ ይህም የመድን ዋስትና ይባላል፡፡ በመድን ተቋማት ውስጥ የተለያዩ ዋስትናዎች አሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ የሕይወት፣ የጤና፣ የአደጋ ዋስትና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ 3.የትምህርት ተቋማት ትምህርት ለሰው ልጆች ንቃተ ሕሊና እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። የትምህርት ተቋማት ትምህርት በተለያየ መልኩ የሚሰጥባቸውና በተለያየ ዕድሜ ላይ ያሉ ሰዎች ዕውቀት የሚያገኙባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡ በተቋማቱ የሚሰጠው ትምህርት ዕውቀትን፣ ክህሎትን፣ ዕሴቶችን፣ ሥነ ምግባርን፣ እምነቶችን እና ልምዶችን ለማሳደግ ይጠቅማል። በሀገራችን የሚገኙ የትምህርት ተቋማት የሕፃናት እንክብካቤ፣ የቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤት፣ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን፣ ዩኒቨርሲቲዎችና የመሳሰሉት የትምህርት ተቋማት በመባል ይታወቃሉ፡፡ 4.የጤና ተቋማት ጤና ማለት የተሟላ አካላዊ፣ አእምሮአዊ እና ማኅበራዊ ደኅንነትና የመሳሰሉትን ያመለክታል፡፡ በሀገራችን ሰዎች ጤንነታቻውን የሚከታተሉባቸው በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የጤና ተቋማት አሉ፡፡ በሕክምና ተቋማት ውስጥ የታመሙ ሰዎች የሚታከሙበት፣ ነፍሰጡር እናቶች የወሊድ ክትትል የሚያደርጉበት ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ በዚህ መሠረት የሕክምና ተቋማት መለስተኛ ክሊኒክ፣ ጤና ጣቢያ፣ ሆስፒታል በመባል ይታወቃሉ፡፡ 127 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ 4.5 የባህል ብዝኀነትና የብዝኀ ሕይወት መሠረቱና ታሪኩ ተግባር- የቡድን ጭውውት 4.5 ተማሪዎችከ 3-4 ሆነው የተለያዩ የብሔርብሔረሰቦችን የሚወክሉ በደስታ ጊዜ (በሠርግ) የሚደረጉ ጭፈራዎችን፣ ወጎችንና የመሳሰሉ የሚከናወኑ ማኅበራዊ እሴቶች በመጠቀም የባህል ብዝሃነትን በጭውውት መልክ ሰርታችሁ ለክፍል ጓደኞቻችሁና ለመምህራችሁ አሳዩ፡፡ ባህል በኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚያከናውኑት የማኅበራዊ፣ የምጣኔ ሀብታዊና የፓለቲካዊ አስተዳደር፣ የሥነ ምግባር፣ የሥነ ልቦና ሁኔታዎች፣ የቋንቋ፣ የታሪክ፣ የሥነ ቃል፣ የምግብ አዘገጃጀት፣ የአመጋገብ ሥርዓት፣ የቤት አሠራር፣ አልባሳት፣ ጌጣጌጦች፣ ባህላዊ እምነቶችና ሌሎችም እሴቶች የሕዝቦች የባህል አካል ተደርገው ይወሰዳሉ። ባህል ከወሊድ፣ ከጋብቻና ከሞት ጋር የተያያዙ ሥነ ሥርዓቶችና ጉርብትናን የመሳሰሉ ማኅበራዊ የትብብር መርሆዎች፣ ባህላዊ የጤና አጠባበቅ ዘዴዎች፣ ባህላዊ የማኅበረሰብ አስተዳደሮችና ሌሎች የማኅበረሰብ ገጽታዎችንም ይጨምራል። ባህል ስንል ማኅበረሰቡ የኔ የሚለውን ማንነቱን የሚገልጽበት ቁሳዊ፣ መንፈሳዊና ቃላዊ ሀብቶቹ ናቸው፡፡ በዚህ መሠረት የተረትና አፈታሪክን የሚያጠቃልለው የቃላዊ ሀብት፣ ዕደ ጥበብን፣ ኪነ-ሕንጻን፣ አልባሳትን፣ ምግብና መጠጥን የሚያጠቃልለው ቁሳዊ ባህል ይባላል፡፡ ሙዚቃን፣ ውዝዋዜንና ተውኔቶችን የሚያጠቃልለው ሀገራዊ ክዋኔ ዘርፍ፣ ክብረ በዓላትንና የሕይወት ዑደትን የሚያካትተው ሀገረሰባዊ ልማድ፣ የቁጥሮችን፣ የቀለሞችንና የምልክቶችን ትርጓሜና አንድምታ የሚመለከተው ማኅበረሰባዊ ውክልና እንዲሁም የእርቅ፣ የአውጫጭኝና የገዳ ሥርዓቶች ማኅበረ ፓለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ይካተታሉ፡፡ የባህል ብዝኀነት የሚለው ቃል የተለያዩ ባህሎች አንዳቸው የሌላውን ልዩነት ማክበርን ሊያመለክት ይችላል። ከዚህም በላይ ብዙውን ጊዜ በአንድ የተወሰነ ክልል ውስጥ ወይም በአጠቃላይ በዓለም ውስጥ ያሉትን የተለያዩ የማህኅበረሰቦችን ወይም ባህሎችን ለመጥቀስ ያገለግላል። ኢትዮጵያ የብዙ ብሔርና ብሔረሰቦች፣ የባህላዊ እሴቶች፣ የጥንታዊ የቋንቋና የታሪክ ባለቤት መሆኗ ይታወቃል። በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የተመዘገቡ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ተፈጥሯዊና ባህላዊ 128 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ ቅርሶች ባለቤትም ናት። ኢትዮጵያ በየማኅበረሰቡ የሚከወኑ ቀደምት ባህላዊ እሴቶችና ትውፊቶች፣ የሥነ- ጽሑፍ፣የኪነ- ሕንጻ፣ የሙዚቃና ሌሎች የኪነ-ጥበብ ሥራዎች መገኛ ጭምር ናት። ስለዚህም የባህል ብዝኀነት የሀገራችን አንዱ መገለጫ ነው፡፡ መልመጃ 4.3 በ ‘ሀ’ ረድፍ ያሉትን ባህላዊና ዘመናዊ ተቋማትን በ ‘ለ’ ረድፍ ከሚገኙ ከትክክል ተግባሮቻቸው ጋር አዛምዱ፡፡ ሀ ለ. 1. ዕድር ሀ. ባህላዊ የቁጠባ ዘዴ 2. ዕቁብ ለ. ቦለቅያ 3. መድን ሐ. የጤና ዋስትና 4. ባህላዊ የውበት መጠበቂያ መ. ዘመናዊ የቁጠባ ዘዴ 5. ባንክ ሠ. ኃዘንተኛን ማጽናናት 4.6 ዓበይት የምጣኔ ሀብት ዘርፎች በኢትዮጵያ ከንዑስ ርዕሱ የሚጠበቀው አጥጋቢ የመማር ብቃት ተማሪዎች ይህን ትምህርት ተምራችሁ ስታጠናቅቁ፡- በኢትዮጵያ የሚገኙ ዓበይት ምጣኔ ሀብታዊ ዘርፎችን ትለያላችሁ፡፡ ቁልፍ ቃላት ግብርና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ትራንስፖርት ንግድ የማነቃቂያ ጥያቄ 1. ግብርና ምንድን ነው? 2. ግብርና የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ዋልታ ነው ሲባል ምን ማለት ነው? ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ በአንድ ሀገር ወይም አካባቢ ሰዎች መደበኛ ሕይወታቸውን ለመምራት ምርትን የሚያመርቱበት፣ የሚያሰራጩበት እና ለፍጆታ የሚያውሉበት ሂደት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚከተሉት የምጣኔ ሀብት ዘርፎች ላይ ተሰማርቶ 129 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ ይገኛል፡፡እነርሱም፡- ግብርና፣ ማዕድን ቁፋሮ፣ ኢንዱስትሪ፣ ንግድ፣ ትራንስፖርት እና ቱሪዝም ናቸው፡፡ ሀ.ግብርና ግብርና ሰብል ማምረት እና ከብት ማርባትን ወይም ሁለቱንም ቀይጦ ማካሄድን የሚያጠቃልል ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ነው፡፡ የዶሮ እርባታ፣ የንብ ማነብ እና የመሳሰሉትንም ያካትታል፡፡ ግብርና የኢትዮጵያ ዋነኛው የምጣኔ ሐብታዊ ዘርፍ ነው፡፡ ከአጠቃላይ የሕዝብ ብዛት ከሰማኒያ በመቶ በላይ የሚሆነው በዚህ ዘርፍ ይተዳደራል፡፡ በተጨማሪም ግብርና በተለየዩ የአየር ንብረት አካባቢዎች የሚከናወን ሲሆን ለእንቅስቃሴውም ልዩ ልዩ ግብዓቶችን የሚፈልግ ዘርፍ ነው፡፡ ግብርና ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ ምርቶችን እና ለኢንዱስትሪ ምርቶች ጥሬ ዕቃ በማቅረብ ወሳኝ ምጣኔ ሐብታዊ ሚና ይጫወታል፡፡ ስለዚህም ግብርና ለሌሎች የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴዎች መሰረት በመሆን ያገለግላል፡፡ በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የግብርና ዓይነቶች በሦስት ይከፈላሉ፡፡ እነርሱም፡- 1. የሰብል ምርት፣ 2. የከብት እርባታ እና 3. ቅይጥ ግብርና ናቸው፡፡ 1. የሰብል ምርት፡- በኢትዮጵያ የሚመረቱ ዋነኞቹ የሰብል ምርቶች ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ በቆሎ፣ ማሽላ እና ዘንጋዳ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጥራጥሬዎች አተር፣ ባቄላ፣ እና ምስር እንዲሁም የቅባት እህሎች ኑግ፣ ሱፍ፣ ተልባ፣ ሰሊጥ፣ ጉሎ፣ እና ለውዝ ይመረታሉ፡፡ 2. የከብት እርባታ፡- ኢትዮጵያ ብዙ የከብት ሀብት አላት፡፡ ነገር ግን ሀብቱ በተገቢና በተለይ በቀንድ ከብት በዘመናዊ መንገድ ስላልተያዘ ብዙ ጥቅም አያስገኝም፡፡ 3. ቅይጥ ግብርና፡- የሰብል ምርትን እና የከብት እርባታን በአንድ ላይ በማቀናጀት የሚተገበር የግብርና ዓይነት ነው፡፡ በኢትዮጵያ 80 ከመቶ የሚደርሱ የአርሶ አደሮች ኑሮ የተመሠረተው በቅይጥ ግብርና ላይ ነው፡፡ 130 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ ለ. ማዕድን ቁፋሮ ማዕድን ቁፋሮ ማለት ማዕድናትን ከመሬት በማውጣት መጠቀም ነው፡፡ በኢትዮጵያ በርካታ ማዕድናት ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን በጥቅም ላይ የዋሉት ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው፡፡ ዋና ዋናዎቹም ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል፡፡ ተ.ቁ ማዕድናት የሚገኙበት አካባቢ 1 ወርቅ ደቡብ ኢትዮጵያ በኦሮሚያ ክልል 2 ፕላቲኒየም ወለጋ 3 መዳብ ሰሜን፣ ደቡብ እና ምስራቅ ኢትዮጵያ 4 ብረት ወለጋ፣ ሐረርጌ፣ ትግራይ 5 ጨው ሞያሌ፣ አፋር፣ ባሌ፣ ትግራይ 6 የድንጋይ ከሰል ወለጋ፣ ጎንደር፣ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ 7 የነዳጅ ዘይት ኦጋዴን፣ ጋምቤላ 8 የእንፋሎት ኃይል ስምጥ ሸለቆ ሰንጠረዥ3 በኢትዮጵያ የሚገኙ ማዕድናት እና የሚገኙበት አካባቢ ሥዕል 4.14 በኢትዮጵያ የማዕድን ፍለጋ የሚካሄድባቸው አካባቢዎች 131 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ መልመጃ 4.5 የሚከተሉትን ጥያቄዎች ትክክል ከሆኑ እውነት ትክክል ካልሆኑ ሀሰት በማለት መልሱ፡፡ 1. ግብርና የሌሎች ምጣኔ ሀብት መሠረት ነው፡፡ 2. የዶሮ እርባታ እና የንብ ማነብ የግብርና አካላት ናቸው፡፡ 3. ሦስቱም የግብርና ዓይነቶች ግንኙነት የላቸውም፡፡ ለሚከተሉት ጥያቄዎች አጭር መልስ ስጡ፡፡ 1. ሦስቱ የግብርና ዓይነቶችን በመጥቀስ ልዩነታቸውን አብራሩ፡፡ 2. በኢትዮጵያ የሚገኙ ማዕድናትን በመዘርዘር ምጣኔ ሐብታዊ ፋይዳቸውን በዝርዝር ጥቀሱ፡፡ 3. በኢትዮጵያ ውስጥ የነዳጅ ዘይት የሚገኝባቸውን አካባቢዎች ጥቀሱ፡፡ ሐ. ኢንዱስትሪ ኢንዱስትሪ በግብርና የተገኙ ጥሬ ዕቃዎችን ወይም ሌሎች የተፈጥሮ ሐብትን በመጠቀም ወደ ሌላ የምርት ዓይነት የመለወጥ አገልግሎት የሚሰጥበት ምጣኔ ሐብታዊ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ይህ ምጣኔ ሐብታዊ እንቅስቃሴ የግብርና ውጤቶችን ወይም የተፈጥሮ ሀብትን በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ የመለወጥ ሂደት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች አሉ፡፡ እነርሱም የጎጆ፣ ቀላል እና ከባድ በመባል ይታወቃሉ፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ዋና ዋና የኢንዱስትሪ አካባቢዎች በመባል የሚታወቁት አዲስ አባበ፣ አዳማ፣ ባሕርዳር፣ መቀሌ፣ ሀዋሳ እና ሌሎች የኢንዱስትሪ ፓርኮች ናቸው፡፡ መ.ንግድ ንግድ ማለት በሰዎች መካከል የሚከናወን ዕቃ የመሸጥ እና የመግዛት ሁኔታ ነው:: በኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ዓይነት የንግድ እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ እነርሱም የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ንግድ በመባል ይታወቃሉ፡፡ 1. የሀገር ውስጥ ንግድ- በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄድ የንግድ እንቅስቃሴ ሲሆን ምርቶቹ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ፣ የሚሸጡ እና የሚገዙ ናቸው፡፡ 2. የውጪ ንግድ- በሀገር ውስጥ የሚመረቱትን የእርሻ ውጤቶች ለውጪ ገበያ ማቅረብ እና ከውጪ ሀገር ሸቀጦችን ማስገባት ነው፡፡ 132 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ ሠ.ትራንስፖርት ትራንስፖርት በአምራች እና በተጠቃሚ መካከል እንደ መገናኛ ድልድይ በመሆን ያገለገለ ነገር ግን በኢትዮጵያ ከዘርፉ የምታገኘው ጥቅም ዝቅተኛ ነው፡፡ ትራንስፖርት ባህላዊ ወይም ዘመናዊ ሊሆን ይችላል፡፡ ረ. ቱሪዝም ኢትዮጵያ በበርካታ ተፈጥሮአዊ እና ሠው ሰራሽ የቱሪስት መስህቦች የታደለች ሀገር ናት፡፡ እነዚህ የቱሪስት መስህቦች ለሀገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ፡፡ ከእነዚህ የቱሪስት መስቦች ውስጥ አንዳንዶቹ በዓለም ቅርስነት ተመዝግበዋል፡፡ ቱሪዝም የተለያዩ ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊ እና አካባቢያዊ ጥቅሞች አሉት፡፡ መልመጃ 4.6 ለሚከተሉት ጥያቄዎች አጭር መልስ ስጡ 1. በኢትዮጵያ የሚገኙ ማዕድናትን እና የሚገኙባቸውን አካባቢዎች ጥቀሱ፡፡ 2. ግብርና እና ኢንዱስትሪ ያላቸውን ግንኙነት ግለፁ፡፡ 3. ሁለቱ የንግድ ዓይነቶችን በመግለፅ እያንዳንዳቸውን ምሳሌ በመስጠት አብራሩ፡፡ 4. በአምራች እና በተጠቃሚ መካከል እንደ መገናኛ ድልድይ በመሆን የሚያገለግለው የምጣኔ ሀብት ዘርፍ _______________ነው፡፡ 133 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ 4.7 ግብርና በኢትዮጵያ በምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ላይ የሚኖረው ሚና አጥጋቢ የመማር ብቃት ተማሪዎች ይህን የትምህርት ይዘት ተምራችሁ ስታጠናቅቁ፡- ¾ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የተለያዩ የግብርና ተግባራትንና እንቅስቃሴዎችን በመለየት ትገልጻላችሁ፡፡ በኢትዮጵያ ወደ ውጭ የሚላኩ ዐበይት የግብርና ውጤቶችን ትዘረዝራላችሁ፡፡ የማነቃቂያ ጥያቄ ግብርና የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ዋልታ ነው ሲባል ምን ማለት ነው? ግብርና ለሰዎች መሰረታዊ ፍላጎቶች ማሟያ የተለያዩ ምርቶችን እና ለኢንዱስትሪዎች ጥሬ ግብዓቶችን በማቅረብ በሀገራችን ምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል:: ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የምታገኘው በዋናነት ከግብርና ምርቶች ነው:: ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርባቸው የእርሻ ውጤቶች ዋና ዋናዎቹ ቡና፣ አበባ፣ ቅመማቅመም፣ የቅባት እህሎች፣ ቆዳና ሌጦ፣ የቁም ከብት እና ጥራጥሬዎች ናቸው:: ከሌሎች ሀገራት የምትገዛቸው ሸቀጦች በዋነኛነት የኢንዱስትሪው ጤቶች ናቸው:: ለምሳሌ መኪና፣ ኮምፒዩተር፣ አውሮፕላን፣ ትራክተር፣ የፋብሪካ ማሽኖች እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊ መሬት እና የሰው ኃይል ስላላት የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን ሌሎችን የምጣኔ ሀብት ዘርፎችን ማሻሻል ስለሆነ መንግስትም ሆነ ህዝቡ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ዘርፍ ነው፡፡ 134 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ 4.8 የኢንዱስትሪ ዓይነቶች በኢትዮጵያ አጥጋቢ የመማር ብቃት ተማሪዎች ይህንን ንዑስ ርዕስ ተምራችሁ ስታጠናቅቁ፡- በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችን ፋይዳ ትመረምራላችሁ፡፡ የማነቃቂያ ጥያቄ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የኢንዱስትሪ አይነቶችን ዘርዝሩ፡፡ ኢንዱስትሪ የግብርና ውጤቶችን ወይም የተፈጥሮ ሀብትን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የመለወጥ ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ኢንዱስትሪዎች በሦስት ይከፈላሉ እነሱም፡- ሀ.የጎጆ ኢንዱስትሪ ለ.ቀላል ኢንዱስትሪ ሐ. ከባድ ኢንዱስትሪ ሀ. የጎጆ ኢንዱስትሪ፡- በሰው ልጅ የዕድገት ታሪክ ውስጥ ቀዳማዊ ስፍራ የሚይዙት የጎጆ ኢንዱስትሪዎች ናቸው፡፡ የጎጆ ኢንዱስትሪዎች ቀላል መሣሪያዎችን በመጠቀም ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን ያመርታሉ፡፡ለምሳሌ፦ የቆዳ የልብስ የብረታ ብረት የእንጨት የሸክላ ስራ የመሳሰሉትን ያጠቃልላሉ፡፡ ሥዕል4.15 የእንጨት ሥራ ውጤቶች 135 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ የጎጆ ኢንዱስትሪዎች በገጠርም ሆነ በከተሞች አካባቢ በብዛት ይታያሉ፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያት በትንሽ ቦታና የገንዘብ አቅም ሊቋቋሙ መቻላቸው ነው፡፡ ለ.ቀላል ኢንዱስትሪ፡-ቀላልኢንዱስትሪ በአብዛኛው ለውጭ ገበያ የሚውሉ ምርቶችን የሚያመርቱ ተቋማት ናቸው፡፡ ቀላል ኢንዱስትሪዎች ጥሬ እቃዎቻቸውን ከግብርና እንዲሁም በከፊል ከተዘጋጁ የደንና የማዕድን ሀብቶች ያገኛሉ፡፡ ቀላል ኢንዱስትሪዎች፡- የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች የወረቀት ፋብሪካ የህትመት ፋብሪካ የቆዳ ውጤት ፋብሪካዎች የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን እና መገጣጠሚያዎችን ያጠቃልላሉ፡፡ ሥዕል፡ 4.16 ቀላል ኢንዱስትሪ (ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ) ሐ. ከባድ ኢንዱስትሪዎች ከባድ ኢንዱስትሪዎች በሰፊ ሥፍራ ላይ የሚቋቋሙ ናቸው፡፡ ምርት ለማምረት ትላልቅና ውስብስብ ሥራ የሚያከናውኑ ከባድ የማምረቻ መሣሪያዎችን ይጠቀማሉ፡፡ የጥሬ ሀብት ግብዓታቸውም ብዙ ሲሆን ለእንቅስቃሴያቸውም ከፍተኛ የገንዘብ አቅም እጅግ የሰለጠነ የሰው ኃይል ይፈልጋሉ፡፡ 136 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ ለምሳሌ ከባድ ኢንዱስትሪ የሚባሉት የስሚንቶ ማምረቻ የኬሚካል ማማረቻ የብረታ ብረት ፋብሪካ የመኪናና የባቡር ማምረቻዎችን ያካትታሉ፡፡ ሥዕል 4.17 የስሚንቶ ፋብሪካ ኢንዱስትሪ በምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ላይ የሚኖረው ሚና በኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ የኢንዱስትሪ ዓይነቶች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም የተለያዩ ጥቅሞችን ይሰጣሉ፡፡ የኢንዱስትሪ ዋና ዋና ጥቅሞች (ፋይዳዎች) የሚከተሉት ናቸው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛሉ፡- የተለያዩ ምርቶችን በማምረትና ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ያስችላሉ፡፡ የሥራ እድል ይፈጥራሉ፡- የተለያዩ የእንዱስትሪ ዘርፎች በተስፋፉ ቁጥር የሚሰራ የሰው ሀይል ስለሚያሥፈልጋቸው የስራ እድል ይፈጥራሉ፡፡ ሀገራዊ ምርቶችን እንድንጠቀም ይረዳሉ ፡- በሀገር ውስጥ የተለያዩ ፋብሪካዎች ካሉና የምንፈልገውን ምርት የሚያመርቱ ከሆነ የውጭ ምርቶችን ከመጠቀም ይልቅ በሀገራችን የሚመረቱ ምርቶችን እንጠቀማለን፡፡ ወጪን ይቀንሳሉ፡- የተለያዩ ምርቶችን ከውጪ የማናስገባ ከሆነና በሀገራችን ምርቶች የምንጠቀም ከሆነ ለቀረጥ የምናወጣው ወጪ ይቀንሳል፡፡ ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ላይ ጉልህ ድርሻ አለው፡፡ 137 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ መልመጃ 4.7 I. በሰንጠረዥ ውስጥ የሚገኙትን የሥራ ዘርፎች የኢንዱስትሪ ዓይነታቸውን ለዩ፡፡ የሥራዘርፍ የኢንዱስትሪ ዓይነት የጎጆ ቀላል ከባድ የቆዳ የሸክላ ሥራ የስሚንቶ ማምረቻ የብረታ ብረት የኬሚካል ማምረቻ የወረቀት የእንጨት የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የህትመት I I. ለሚከተሉት ጥያቄዎች አጭር መልስ ስጡ፡፡ 1. የኢንዱስትሪ ጥቅሞችን ዘርዝሩ፡፡ 2. ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ ያለው ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ምንድን ነው? 4.9 የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዓይነቶች በኢትዮጵያ አጥጋቢ የመማር ብቃት ቱሪዝም በኢትዮጵያ የሚኖረውን ፋይዳ ይመረምራሉ የማነቃቂያ ጥያቄ 1. ቱሪዝም ምንድን ነው? 2. በአካባቢያችሁ የሚገኙ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ አይነቶችን ጥቀሱ፡፡ ቁልፍ ቃላት ቱሪዝም መሰህብ ቱሪዝም የሰዎችን ለጉብኝት ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስን ያመለክታል፡፡ ሰዎች በራሳቸው ተነሳሽነት ከአካባቢያቸው በቅርብ ወይም በሩቅ ርቀት የሚገኙትን አስደናቂና 138 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ አስገራሚ ነገሮችን ለማየት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጉብኝት (tourism) ይባላል:: ኢትዮጵያ በቱሪስት መስህቦች የታደለች ሀገር ናት፡፡ ከእነዚህ ውስጥም አንዳንዶቹ በዓለም ሀብትነት የተመዘገቡ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የቱሪስት መስህቦች የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ናቸው፡፡ የተፈጥሮ የቱሪስት መስህብ የሚባሉት የመልከአ ምድር አቀማመጥ ፣ የአየር ንብረት፣ የተለያዩ ዕፅዋትና እንስሳት ይጠቀሳሉ፡፡ ሰው ሠራሽ የቱሪስት መስህብ የሚባሉት ታሪካዊ ቦታዎች፣ የባህል ቅርሶች፣ የዕደ ጥበብ ውጤቶች፣ ቤተመዘክሮች እና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ቱሪዝም ጭስ አልባ ኢንዱስትሪ በመባል ይታወቃል፡፡ 4.10 ቱሪዝም በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚኖረው ሚና በኢትዮጵያ የንዑስ ርዕሱ አጥጋቢ የመማር ብቃት ተማሪዎች ይህን የትምህርት ይዘት ተምራችሁ ስታጠናቅቁ፡- ቱሪዝም በኢትዮጵያ የሚኖረውን ፋይዳ ትመረምራላችሁ፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ ቱሪዝም በማኅበራዊና ኢኮኖማያዊ እንቅስቃሴ ላይ ያለው ሚና በጣም ብዙ ነው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ጥቂቶቹን ስንመለከት i. የውጪ ምንዛሪን ያሳድጋል፡፡ ii. የሀገር ምጣኔ ሀብትን ያሳድጋል፡፡ iii. ለአካባቢው ማኅበረሰብ ሰፊ የሥራ ዕድልን ይፈጥራል፡፡ iv. የሀገርን ባህላዊ እሴቶችን በማስተዋወቅ ለገጽታ ግንባታ ያገለግላል፡፡ v. የተፈጥሮ ሀብታችንን እንድንከባከብ ይረዳናል፡፡ vi. የማኅበረሰቡን ግንኙነት ያጠናክራል፡፡ vii. የተለያዩ ባህሎችን ያቀራርባል፣ ያስተዋውቃል፡፡ 139 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ 4.11 በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ዋና ዋና ጉዳዮች አጥጋቢ የመማር ብቃት ተማሪዎች ይህን የትምህርት ይዘት ተምራችሁ ስታጠናቅቁ፡- በኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ዐበይት ምክንያቶችን ትገልጻላችሁ፡፡ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይ ተፅዕኖ የሚያደርሱ የተለያዩ ተግዳሮቶች አሉ፡፡ ከነዚህ መካከል:- በቱሪዝም ሙያ በቂ የሆነ የሠለጠነ የሰው ኃይል አለመኖር የቱሪዝም መዳረሻዎች የመረጃ እጥረት የመሠረተ ልማት አለመሟላት በተለያዩ ጊዜ የሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎች የተፈጥሮ ደንና የብርቅዬ የዱር እንስሳት መመናመን ደካማ የቱሪዝም መስህቦችን የማስተዋወቅና የገበያ ሁኔታ በዋናነት ይጠቀሳሉ መልመጃ 4.8 ለሚከተሉት ጥያቄዎች አጭር መልስ ስጡ፡፡ 1. በኢትዮጵያ የሚገኙትን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዓይነቶች ውስጥ አራቱን ጥቀሱ፡፡ ሀ. --------------------------------------------------- ለ. --------------------------------------------------- ሐ. -------------------------------------------------- መ. -------------------------------------------------- 2. ቱሪዝም ለሀገራችን ከሚሰጠው ጥቅሞች ውስጥ ሦስት ጥቀሱ፡፡ ሀ. ---------------------------------------------------- ለ. ----------------------------------------------------- ሐ. ---------------------------------------------------- 3. በቱሪዝም ዕድገት ላይ ተፅዕኖ የሚያደርሱ ነገሮችን እንዴት መቀነስ እንደሚቻል አጭር ማስታወሻ በመጻፍ ለመምህራችሁ አቅርቡ፡፡ 140 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ ማጠቃለያ የአንድ ኅብረተሰብ አመለካከት፣ እምነት፣ መጠቀሚያ ቁሳቁስ፣ በዓል አከባበር፣ አመጋገብ፣ አለባበስ፣ ዕደ ጥበብ የመሳሰሉት ባህል በመባል ይታወቃሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የራሳቸው የአለባበስ ፣የአመጋገብ፣ የበዓል አከባበር፣ የለቅሶ ሥነ-ሥርአት፣ የሠርግ ሥነ-ሥርአት፣ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ፣ ባህላዊ ጭፈራዎች አላቸው፡፡ እነዚህን ክንዋኔዎች የባህል ብዝኃነትን ይገልፃሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚነገሩ ቋንቋዎች በሁለት ዋና ዋና የቋንቋ ቤተሰቦች ይመደባሉ:: እነርሱም አፍሮ እስያዊ እና ናይሎ ሰሐራዊ ናቸው፡፡ የአንድ ቅርስ ቅርጽ፣ መጠን፣ ዓይነትና ሥሪት የሚታወቅ ወይም እነዚህን በመጠቀም ሊጠና የሚችል ከሆነ የሚዳሰስ ቅርስ ይባላል፡፡ የማይዳሰስ ቅርስ በዓይን የማይታይና የማይጨበጥ ነገር ግን በድምፅ ወይም በአካላዊ አንቅስቃሴ የሚገለጽ አንድ ሕዝብ በቅብብሎሽ ወይም በትውፊት ያገኘው ሀብት ነው፡፡ ሰዎች መደበኛ ሕይወታቸውን ለመምራት ምርትን የሚያመርቱበት፣ የሚያሰራጩበት እና ለፍጆታ የሚያውሉበት ሂደት ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ይባላል፡፡ ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርባቸው የእርሻ ውጤቶች ዋና ዋናዎቹ ቡና፣ አበባ፣ ቅመማቅመም፣ የቅባት እህሎች፣ ቆዳና ሌጦ፣ የቁም ከብት እና ጥራጥሬዎች ናቸው፡፡ ኢንዱስትሪ የግብርና ውጤቶችን ወይም የተፈጥሮ ሀብትን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የመለወጥ ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ዓይነቶች የጎጆ ኢንዱስትሪ፣ ቀላል ኢንዱስትሪ እና ከባድ ኢንዱስትሪ ናቸው፡፡ ቱሪዝም ሰዎች ለጉብኝት ከቦታ ወደ ቦታ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ያመለክታል፡፡ 141 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ የምዕራፉ ማጠቃለያ ጥያቄዎች I. የሚከተሉትን ጥያቄዎች ትክክል የሆነውን እውነት ትክክል ያልሆነውን ደግሞ ሐሰት በማለት መልሱ፡፡ 1. ባህል የአንድ ማኅበረሰብ መገለጫ አይደለም፡፡ 2. ኢትዮጵያ የብዘኀ ባህልና የብዘኀ ቋንቋ ባለቤት ናት፡፡ 3. ቱሪዝም ከግብርና ጋር ተያያዥነት የለውም፡፡ 4. ቅይጥ ግብርና የሚባለው የሰብል ምርት የሚያሳይ ነው፡፡ 5. የጎጆ ኢንዱስትሪ ቀላል መሣሪያዎችን በመጠቀም ቁሳቁሶችን ያመርታል:: II. በ “ሀ” ስር የተሰጡትን የቋንቋ ቤተሰቦች እና ዋና የቋንቋ ቤተሰብ በ “ለ” ስር ከተዘረዘሩት ቋንቋዎች ጋር አዛምዱ፡፡ ሀ ለ 1. የሴም ቋንቋ ምድብ ሀ. ጉሙዝ 2. የኩሽ ቋንቋ ምድብ ለ. ዶርዜ 3. የኦሞአዊ የቋንቋ ምድብ ሐ. አማርኛ 4. የናይሎ ሰሐራዊ መ. አፋን ኦሮሞ III. ለሚከተሉት ጥያቄዎች ከተሰጡት አማራጮች መካከል ትክክለኛውን መልስ የያዘውን ሆሄ በመምረጥ በተሰጠው ክፍት ቦታ ጻፉ፡፡ 1. ከሚከተሉት ውስጥ የማይዳሰስ ቅርስ የቱ ነው? ሀ. የመስቀል በዓል አከባበር ሐ. የታችኛው የአዋሽ ሸለቆ ለ. የጥያ ትክል ድንጋይ መ. የአክሱም ሀውልት 2. ከሚከተሉት አንዱ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ነው፡፡ ሀ. አሸንድዬ ሐ. የቡሄ ጭፈራ ለ. ፍቼ ጨምበላላ መ. ሶለል 3. በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚከናወኑት የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴዎች ለኢንዱስትሪ በስፋት ግብዓት የሚያቀርበው፡፡ ሀ. ቱሪዝም ለ. ግብርና ሐ. ንግድ መ. ትራንስፖርት 4. ከሚከተሉት ውስጥ ከባድ ኢንዱስትሪ የሆነ የቱ ነው? ሀ. የወረቀት ማምረቻ ሐ. የቆዳ ውጤት ፋብሪካ ለ. የሲሚንቶ ማምረቻ መ. የብረታ ብረት ፋብሪካ 142 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ 5. ከሚከተሉት ውስጥ የቱሪዝም ጥቅም የቱ ነው? ሀ. የውጭ ምንዛሬን ያሳድጋል ሐ. የማህበረሰቡን ግንኙነት ያጠናክራል ለ. የሀገር ምጣኔ ሀብትን ያሳድጋል መ. ሁሉም መልስ ነው 6. ከሚከተሉት ውስጥ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የማያስገኘው የግብርና ምርት የቱ ነው? ሀ. ቡና ለ. ስንዴ ሐ. ሰሊጥ መ. አበባ 7. በኢትዮጵያ በጣም የተለመዱ ባህላዊ ክዋኔዎች ያልሆነ የቱ ነው? ሀ. የቡሄ ጨዋታ ለ. የውሃ ቀን ሐ. አሸንዳ መ. ሻደይ 8. ተፈጥሮአዊ የቱሪስት መስህብ ከሚባሉት አንዱ የቱ ነው? ሀ. የአየር ንብረት ሐ. ቤተ መዘክር ለ. የዕደ ጥበባት ውጤቶች መ. የባህል ቅርሶች IV. ለሚከተሉትን ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ ስጡ፡፡ 1. በዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡ የማይዳሰሱ ቅርሶች ውስጥ ሦስቱን ጥቀሱ፡፡ ሀ. ___________________________________ ለ. ___________________________________ ሐ. ___________________________________ 2. በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ከሚነገሩ ቋንቋዎች ውስጥ አራቱን ጥቀሱ፡፡ ሀ. ___________________________________ ለ. ___________________________________ ሐ. ___________________________________ መ. ___________________________________ 3. በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚዳሰሱ ቅርሶች አራቱን ጥቀሱ፡፡ ሀ. ___________________________________ ለ. ___________________________________ ሐ. __________________________________ መ. __________________________________ V. ለሚከተሉትን ጥያቄዎች አጭር መልስ ስጡ፡፡ 1. ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ላይ ያለውን ሚና አብራሩ:: 2. በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ዋና ዋና ጉዳዮች ዘርዝሩ፡፡ 3. ሰዎች ባህላቸውን ለማስተዋወቅ የሚጠቀሙትን ዘዴዎች ጥቀሱ፡፡ 143 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አራት የባህል ብዝኀነት በኢትዮጵያ ፍትሻ ልታከናውኗቸው የምትችሏቸውን ተግባራት ለመግለጽ ይህን() ምልክት በሳጥኖቹ ውስጥ በማኖር አመልክቱ፡፡ ¾ የኢትዮጵያን የባህል ብዝኀነት ዋጋ እሰጣለሁ፡፡ ¾ በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ የባህል ክዋኔዎችን እለያለሁ፡፡ ¾ በኢትዮጵያ የሚገኙ ዋና ዋና የቋንቋ ቤተሰቦችን እዘረዝራለሁ፡፡ ¾ በኢትዮጵያ የሚገኙ ባህላዊ ቅርሶችን በመለየት አብራራለሁ፡፡ ¾ በኢትዮጵያ የሚገኙ ባህላዊና ዘመናዊ ተቋማትን በመለየት አስፈላጊነታቸውን እገልጻለሁ፡፡ ¾ በኢትዮጵያ የሚገኙ ዐበይት ምጣኔ ሀብታዊ ዘርፎችን እለያለሁ፡፡ ¾ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የተለያዩ የግብርና ተግባራትንና እንቅስቃሴዎችን በመለየት እገልጻለሁ፡፡ ¾ በኢትዮጵያ ወደ ውጭ የሚላኩ ዐበይት የግብርና ውጤቶችን እዘረዝራለሁ፡፡ ¾ በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችን ፋይዳ እመረምራለሁ፡፡ ¾ ቱሪዝም በኢትዮጵያ የሚኖረውን ፋይዳ እመረምራለሁ፡፡ ¾ በኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ዐበይት ምክንያቶችን እገልጻለሁ፡፡ የቃላትፍቺ የሚዳሰሱ ቅርሶች------------በዓይን የሚታዩ ቅርሶች የማይዳሰሱ ቅርሶች-----------በዓይን የማይታዩ (ረቂቅ) ቅርሶች ማህበራዊ አካባቢ-------------ሰዎች እለት ተለት የሚያከናውኗቸው ተፈጥሯዊ ያልሆኑ ተግባራት ኢንዱስትሪ---------------------የማምረቻ ቦታዎች ቅይጥ ግብርና------------------የሰብል ምርትና የከብት እርባታ ማነብ..................................ንብ ማርባት 144 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አምስት ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ምዕራፍ አምስት ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ከምዕራፉ የሚጠበቁ አጥጋቢ የመማር ውጤቶች ተማሪዎች ይህንን ምዕራፍ ተምራችሁ ስታጠናቅቁ ፡- አደገኛ ኬሚካልንና አደንዛዥ ዕፅን ትለያላችሁ፡፡ ዋና ዋና ሱስ አምጪ ዕፆችን ትለያላችሁ፡፡ በወረዳችሁና በክፍለ ከተማችሁ የሚገኙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ትለያላችሁ፡፡ የድርቅና የረሃብ ምንነትን ትለያላችሁ፡፡ በኢትዮጵያ ለሚታየው የድርቅ መንሥኤና ውጤት ትገልፃላችሁ፡፡ ለድርቅ ተጋላጭ ቦታዎችን ትለያላችሁ፡፡ በከተማችሁ ድርቅን ለመቋቋም የሚያስችሉ ዘዴዎችን ትዘረዝራላችሁ፡፡ ድርቅ የግድ ረሃብን ተከትሎ የማይከሰትባቸውን ምክንያቶች ትገልጻላችሁ፡፡ በኢትዮጵያ ድርቅን ለመቋቋም የሚያገለግሉ ሀገር በቀል ዘዴዎችን ትዘረዝራላችሁ፡፡ 145 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አምስት ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች የምዕራፉ ዋና ዋና ይዘቶች 5.1 ኤች.አይ. ቪ/ ኤድስ በኢትዮጵያ 5.2 በወረዳችን የሚገኙ ኬሚካሎችና ተገቢነት የሌላቸው የመድኃኒት አጠቃቀም 5.3 በከተማችን የሚገኙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች 5.4 ድርቅና ረሃብ መግቢያ ተማሪዎች በ4ኛ ክፍል የአካባቢ ሳይንስ ትምህርታችሁ ስለ ኬሚካል አጠቃቀም ደኅንነት፣ ኤች አይ ቪ እና ሌሎች ተላላፊ ሕመሞች እንዲሁም ስለ ድርቅና ረሃብ ተምራችኋል፡፡ በዚህ ምዕራፍ ደግሞ በኢትዮጵያ የተለያዩ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች የሚባሉትን ኤች አይ ቪ ኤድስ፣ ኬሚካሎች እና ተገቢነት የሌላቸው መድሐኒቶች፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች፣ እንዲሁም ስለ ድርቅ እና ረሀብ ትማራላችሁ:: እነዚህ ጉዳዮች በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማህበራዊ እና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የተለያዩ ተፅዕኖዎችን ያሳርፋሉ:: እነዚህን ተፅዕኖዎች ለመቋቋም የጉዳዮቹን መንስኤ፣ የሚያስከትሉትንም ተፅዕኖ እና መከላከያ ዘዴዎችን ትማራላችሁ፡፡ ይህ ምዕራፍ ሲጠናቀቅ የሚጠበቅባችሁን እውቀት እና ክህሎት አዳብራችሁ ለመገኘት እንድትችሉ በንቁ ተሳታፊነት ትምህርቱን መከታተል ይጠበቅባችኋል፡፡ ይህን በሚታደርጉበት ጊዜ እንዲሁም የተለያዩ ውይይቶችን በምታደርጉበት ወቅት አብሮ የመስራት እና የሀገር ፍቅር እሴቶችን ታዳብራላችሁ፡፡ 146 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አምስት ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች 5.1 ኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ በኢትዮጵያ ቁልፍ ቃላት ኤች አይ ቪ ኤድስ የቡድን ውይይት 5.1 የመወያያ ጥያቄ በአራተኛ ክፍል የአካባቢ ሳይንስ ትምህርት ስለ ኤች አይ ቪ የተማራችሁትን በማስታወስ በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያይታችሁ የደረሳችሁበትን ድምዳሜ ለመምህራችሁ ተናገሩ፡፡ 1. የኤች አይ ቪ እና የኤድስ ልዩነት ምንድን ነው? 2. የኤች አይ ቪ ኤድስ መተላለፊያና መከላከያ መንገዶችን ዘርዝሩ፡፡ ኤች አይ ቪ የሰውን ነጭ የደም ህዋስ የሚያጠቃ ቫይረስ ነው፡፡ ይህ ቫይረስ ወደ ደም ከገባ በኋላ የነጭ የደም ህዋስ ቁጥርን እነዲቀንስ በማድረግ ሰዎችን ለልዩ ልዩ በሽታዎች ያጋልጣል፡፡ ነጭ የደም ህዋስ ሲቀንስ ሰዎች ለልዩ ልዩ በሽታዎች ይጋለጣሉ፡፡ይህ ደረጃ ኤድስ ይባላል፡፡ ኤድስ በኤች አይ ቪ ቫይረስ የሚመጣ በሽታ ሲሆን የሰውን በሽታ የመከላከል አቅም ይቀንሳል፡፡ የኤድስ መተላለፊያ ዋና ዋና መንገዶች የሚከተሉት ናቸው፡፡ እነርሱም፡- 1. ጥንቃቄ የጎደለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት- የኤች አይ ቪ ቫይረስ ያለበት ሰው ያለጥንቃቄ ከሌለባቸው ሰዎች ጋር የግብረስጋ ግንኙነት ካደረገ ቫይረሱ ይተላለፋል 2. በደም ንክኪ- የሰውነታችን ክፍል በመቁሰል ቢደማ እና ከሌሎች ጋር ንክኪ ቢፈጥር የኤች አይ ቪ ቫይረስ ይተላለፋል፡፡ 3. ከእናት ወደ ልጅ በወሊድ ጊዜ በደም ንክኪ ወይም ጡት በማጥባት ይተላለፋል 4. የተበከሉ ሹልና ስለታም ነገሮችን በመጠቀም ሊተላለፍ ይችላል፡፡ 147 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አምስት ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያ መንገዶች፡- 1. መታቀብ፡- ከጋብቻ በፊት ከግብረ ሥጋ ግንኙነት አለመፈጸም፣ 2. ሹልና ስለታም መሣሪያዎችን በጋራ አለመጠቀም፣ 3. የጥርስ ብሩሽ በጋራ አለመጠቀም፣ 4. የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎችን ከተገለገልንበት በኋላ በአግባቡ ያለማስወገድ፣ 5. ከቫይረሱ ጋር የምትኖር ነፍሰ ጡር ቫይረሱ በእርግዝና ወቅት ወደ ጽንሱ እንዳይተላለፍ የቅርብ ሕክምና ክትትል ማድረግ 6. የፀጉር መቁረጫ ማሽን በሚገባ ሳይፀዳ በጋራ አለመጠቀም ናቸው፡፡ ኤድስን ለመከላከል የሚያስችሉ የህይወት ክህሎቶች የህይወት ክህሎት የህይወት ክህሎት ማለት ተማሪዎች ከኤች አይ ቪ ኤድስ ጋር በተያያዘ መተግበር የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ አነዚህን የሚተገበሩ ጉዳዮች የህይወት መመሪያ አድርጎ መመልከት ጠቃሚ ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ፡- 1. ከቤተሰብና ከመምህራን ጋር ግልፅ ውይይት ማድረግ 2. በት/ቤቱ ፀረ-ኤድስ ክበብ መሳተፍ 3. የቤተሰብና የመምህራንን ምክር ማዳመጥና መተግበር 4. ራስን ለኤች አይ ቪ ቫይረስ ከሚያጋልጡ ድርጊቶች መጠበቅ 5. በጓደኛና በሌሎች ሰዎች አጉል ምክር አለመገፋፋት እና ሌሎች ሰዎች በሚፈፅሟቸው መጥፎ ድርጊቶች አለመሳተፍ 6. ስለቫይረሱ ራስን ማስተማር 7. ለኤች አይ ቪ ቫይረስ ከሚያጋልጡ ተግባራት ራስን ማራቅ ናቸው፡፡ የቡድን ውይይት 5.2 ኤች.አይ.ቪ./ ኤድስ በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርሰውን ጫና መረጃዎችን ከተለያዩ ምንጮች ፈልጋችሁ ተወያዩበት፡፡ የደረሳችሁበትን ድምዳሜ በተወካዮቻችሁ አማካኝነት ለክፍል ጓደኞቻችሁ አቅርቡ፡፡ 148 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አምስት ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች በኢትዮጵያ ኤች አይ ቪ ኤድስ የተለያዩ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ከሚያስከትላቸው ችግሮች ዋና ዋናዎቹ፡- 1. ማህበራዊ ቀውስ- ኤች አይ ቪ/ ኤድስ ያለባቸው ሰዎች በማህበረሰቡ ዘንድ መገለል ያጋጥማቸዋል፡፡ ይህ ችግር ስላለ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ራሳቸውን ደብቀው ይኖራሉ፡፡ ይህ ደግሞ የቫይረሱን ስርጭት ያባብሰዋል፡፡ 2. ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ- ኤች አይ ቪ በአብዛኛው የሚያጠቃው አምራች ኃይሉን በመሆኑ ከስራ ማቋረጥና የገቢ መቀነስን ያስከትላል፡፡ 3. የተማሪዎች ከት/ቤት ማቋረጥ- የተማሪዎች ወላጆች ወይም አሳደጊዎች በቫይረሱ መጠቃት ተማሪዎቹ የሚረዳቸው ስለማይኖር ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ይገደዳሉ፡ 4. ልጆች ወላጅ አልባ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ መልመጃ 5.1 ለሚከተሉት ጥያቄዎች አጭር መልስ ስጡ፡፡ 1. የኤች አይ ቪ/ኤድስ መተላለፊያ መንገዶችን ዘርዝሩ፡፡ 2. የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከያ መንገዶችን ጥቀሱ፡፡ 3. ኤች አይ ቪ ኤድስ የሚያስከትላቸው ችግሮች ምንድን ናቸው? 149 Fetena.net : Ethiopian No#1 Educational Resource ምዕራፍ አምስት ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች 5.2 በወረዳችን የሚገኙ ኬሚካሎችና ተገቢነት የሌላቸው የመድኃኒት አጠቃቀም አደንዛዥ ዕፅ እና የኬሚካል አጠቃቀም ደህንነት አጥጋቢ የመማር ብቃት ተማሪዎች ይህን ትምህርት ተምራችሁ ስታጠናቅቁ፡- ዋና ዋና ሱስ አምጪ ዕፆችን ትለያላችሁ፡፡ ኬሚካልንና አደንዛዥ ዕፅን ትለያላችሁ፡፡ ቁልፍ ቃላት ሱስ አምጭ አደንዛዥ ዕፅ አደገኛ ከሚካል የቡድን ውይይት 5.3 ዓላማ- ኬሚካሎች እና አደንዛዥ ዕፆ