መሠረተ ሀይማኖት ስምንተኛ ክፍል PDF

Document Details

WellBoron

Uploaded by WellBoron

Chercher Polytechnic College

Tags

Amharic religious studies Christianity

Summary

This document seems to be a textbook or study guide focusing on religious teachings, specifically for the eighth grade in Ethiopia. It covers the concept of salvation and the origin of sin within a religious perspective.

Full Transcript

መሠረተ ሀይማኖት ስምንተኛ ክፍል ነገረ ድኅነት መሠረተ ሀይማኖት ስምንተኛ ክፍል መክሥተ አርዕስት መግቢያ............................................................................................................................................................ 3 ምዕራፍ አንድ...

መሠረተ ሀይማኖት ስምንተኛ ክፍል ነገረ ድኅነት መሠረተ ሀይማኖት ስምንተኛ ክፍል መክሥተ አርዕስት መግቢያ............................................................................................................................................................ 3 ምዕራፍ አንድ..................................................................................................................................................... 4 ፩.፩. ነገረ ድኅነት የቃሉ ትርጉም.......................................................................................................................... 4 ፩.፪. ነገረ ድኅነት በቅዱሳት መጻሕፍት................................................................................................................... 5 ፩.፫. የአዳም አወዳደቅ...................................................................................................................................... 6 ፩.፫.፩. አዳም ወደቀ ስንል ምን ማለታችን ነው?.................................................................................................... 7 ፩.፫.፩. ለአዳም መሳሳት ተጠያቂው ማን ነው ?..................................................................................................... 8 ምዕራፍ ኹለት.................................................................................................................................................. 10 ፪.፩. ያዳነን ማን ነው?..................................................................................................................................... 10 ፪.፪. ሰው የዳነው ከምንድነው ?......................................................................................................................... 13 ፪.፫. በነገረ ድኅነት ውስጥ የሰው ልጅ ድርሻ......................................................................................................... 14 ፪.፬. ወላዲተ አምላክ በነገረ ድኅነት ውስጥ ያላት ሱታፌ.......................................................................................... 16 ምዕራፍ ሦስት.................................................................................................................................................. 18 ፫.፩. በነገረ ድኅነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች እና መልሶቻቸው...................................................................................... 18 ፫.፩.፩. ድኅነት በጸጋ ብቻ ነውን ?.................................................................................................................. 18 ፫.፩.፪. ድኅነት በእምነት ብቻ ነውን ?............................................................................................................. 19 ፫.፩.፫. ሕግን ሳይጠብቁ መጽደቅ / መዳን / ይቻላል ?........................................................................................ 20 ፫.፩.፬. ድኅነት ቅጽበታዊ ወይስ ሒደታዊ ?...................................................................................................... 21 ዋቢመጻሕፍት.................................................................................................................................................. 23 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ/ሰ/ት/ ቤቶች ማደራጃ መምሪያ 2 የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት መሠረተ ሀይማኖት ስምንተኛ ክፍል መግቢያ ነገረ ድኅነት ስለሰው ልጆች ድኅነት የሚነገርበት የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት ከመሆኑም በላይ የቤተ ክርስቲያትን ትምህርቶች ሁሉ ማዕከልና መሠረት ነው። የሰው ልጅ ትዕዛዘ እግዚአብሔርን በማፍረሱ ምክንያት ከእግዚአብሔር ኀብረት ተለይቶ በዲያብሎስ ቁራኝነት ተይዞ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመናት ኖሯል። ሆኖም ግን በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ የሰው ልጅ ፍላጎት ድኅነትን ማግኘት ስለነበር የመዳን ተስፋውን ከፈጣሪው ተቀብሎ በተስፋ ይጠባበቅ ነበር። እግዚአብሔር በሰጠው የመዳን ተስፋ መሠረት በነቢያት ትንቢት ተነግሯል ሱባዔም ተቆጥሯል። ታዲያ የሰው ልጅ ከደረሰበት ውድቀት ለመዳን መሥዋዕት ቢያቀርብም ጸሎት ቢያደርስም እርሱ ባቀረበው መሥዋዕት ባደረሰው ጸሎት የነበረበትን ዕዳ መሠረዝ ግን አልተቻለውም። (ኢሳ ፷፬፥፮) ስለሆነም እግዚአብሔር አምላካችን ለአዳም በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ድኅነት የናፈቀውን ፣ መከራ ያስጨነቀውን የሰውን ልጅ ያድነው ዘንድ ነቢያት በተናገሩት ትንቢት ፣ በቆጠሩት ሱባዔ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ ። ድኅነት ርቆት መከራ በዝቶበት መዳን ሲፈልግ ከነበረው ሥጋ ጋር ሕይወት የሚሰጠው አዳኝ ይኾነው ዘንድ መለኮት ተዋሐደ። ድኅነት አጥቶ ሲሰቃይ ለነበረው የሰው ልጅ ፈጣሪ የተዘጋ ርስቱን ፣ የተቀማ ልጅነቱን ፣ ያጣውን አንድነቱን መለሰለት ። ስለዚህም የምሥራች ተነገረ ድኅነት ተበሠረ በዚህም የሰው ልጅ ተጠመቆ ልጅነቱን ድጋሚ የሚያገኝበት ጸጋ ተጎናጸፈ ፣ የነቢያት ትንቢትም ተፈጸመ። ይህ ሁሉ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ጠፍተው እንዳይቀሩ ያለውን ፍቅር የገለጸበት የፍቅር መንገድ ነው። በዚህ ክፍል የመሠረተ ሃይማኖት ትምህርት የነገረ ድኅነትን ነገር በሰፋና በጎላ መልኩ የምንመለከት ይሆናል ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ/ሰ/ት/ ቤቶች ማደራጃ መምሪያ 3 የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት መሠረተ ሀይማኖት ስምንተኛ ክፍል ምዕራፍ አንድ ዓላማ ተማሪዎች ይህንን ምዕራፍ ተምረው ሲያጠናቅቁ ፦ ፩ የነገረ ድኅነት ትርጉም እና የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በነገረ ድኅነት ምን እንደሆነ ይረዳሉ ። ፪ ቅዱሳት መጻሕፍት ስለ ነገረ ድኅነት የሚሰጡትን ምሥክርነት ተረድተው ምሥክሮች ይሆናሉ። ፫ የሰው ልጅ የወደቀው እንዴት እና በምን ምክንያት እንደሆነ በመረዳት ከክፉ ምክር ራሳቸውን ይጠብቃሉ ። የማስጀመሪያ ጥያቄ ፩ የሰው ልጅ በመውደቁ ምክንያት ያጣቸው ነገሮች ምን ምን ናቸው ? ፪ ለሰው ልጅ ውድቀት ተጠያቂው ማን ነው ? ፫ ስለነገረ ድኅነት ከቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃ የሚሆኑ ጥቅሶችን አቅርቡ። ፩.፩. ነገረ ድኅነት የቃሉ ትርጉም ነገረ ድኅነት “ነገር” እና “ድኅነት” ከሚሉ ኹለት ቃላት የተገኘ ሲሆን “ነገር” የሚለው ቃል በቤተ ክርስቲያን ትምህርት የአንድን ትምህርት መስክ ከመነሻው እስከ መድረሻው ያለውን የሚያስረዳ (መግለጫ) ሆኖ የሚያገልግል ቃል ነው። ለምሳሌ ፦ ነገረ ማርያም ስንል ስለ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለሰው ልጅ በእግዚአብሔር ፈቃድ የተገለጠውን ሁሉ የምንማርበት ትምህርት ነው። በተመሳሳይ እንደ ነገረ ቅዱሳን ፣ ነገረ ሃይማኖት፣ ነገረ ቤተ ክርስቲያን ፣ ነገረ መላዕክት እና የመሳሰሉትን ብንመለከት ከመነሻቸው እስከ መድረሻቸው ያለውን የሚገልጽ (የሚያስረዳ) ቃል ነው። ድኅነት ማለት ደግሞ ከክፉ ነገር ሁሉ መዳን በሚል የሚተረጎም ሲሆን በቤተ ክርስቲያን ትምህርት እንደ አገባቡ ከተለያየ ነገር ስለመዳን ተገልጾ እናገኘዋለን። ለምሳሌ ፦  በኖኅ ዘመን ከመጣው የጥፋት ውኃ ኖኅ ከነቤተሰቡ ከሞት ድኗል፤ ዘፍ ፮፥፱  ሎጥ ወደ ሰዶም ምድር በኃጢአት ምክንያት ከመጣው እሳት ድኗል፤ ዘፍ ፲፱  ያዕቆብና ልጆቹ በዘመኑ ከነበረው ከባድ ረሀብ በዮሴፍ ምክንያት ድነዋል፤ ዘፍ ፵፮  ሶሪያዊው ንዕማን ከነበረበት ለምጽ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቆ ድኗል፤ ፪ኛ ነገ ፭  ሕዝበ እስራኤል ከሐማ ተንኮል በጾምና ጸሎት ድነዋል ፤ መ.አስ ፰  ሕዝበ እስራኤል በሙሴ አማካኝነት ከግብጽ ባርነት ነጻ በመውጣት ድነዋል፤ ዘፍ ፲፰፥፲  ሐዋርያት በጀልባ ሳሉ ማዕበል ሲነሳ ጌታን አድነን በማለት ድነዋል፤ ማቴ ፰  ቅዱስ ጳውሎስ ታስሮ ወደ ሮም ሲሔድ ከደረሰው አደጋ ድኗል ፤ ሐዋ ፳፯፥ ፴፩  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዚህ ምድር ሲመላለስ ከተለያየ ችግር እና ደዌ የፈወሳቸው ብዙ ሰዎች ነበሩ። ማቴ ፰ ፥ ፭ ፤ ሉቃ ፰,፥፵፫ ፣ ዮሐ ፭፥ ፩ -፲፭ ፤ ዮሐ ፱ በአጠቃላይ ከላይ የተመለከትናቸው በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ መዳን ተብለው ተገልጸዋል ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ/ሰ/ት/ ቤቶች ማደራጃ መምሪያ 4 የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት መሠረተ ሀይማኖት ስምንተኛ ክፍል በነገረ ድኅነት ትምህርት (መዳን) ስንል እነዚህን ከላይ የተመለከትናቸውን ማለታችን አይደለም። እነዚህ ሁሉ የተጠቀሱት ድኅነቶች ጊዜያዊና ምድራዊ ድኅነቶች ነበሩ ። በነገረ ድኅነት መዳን ስንል የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ በማፍረሱ ምክንያት ከደረሰበት ውድቀት ከጸጋ መራቆት ፤ የባሕርይ መጎሳቆል በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያገኘውን ድኅነት ማለታችን ነው። ይህም ድኅነት የሚከተሉትን አራት መሠረታዊ የእግዚአብሔር ስጦታዎችን ያጠቃልላል። እነርሱም ፦  ከኃጢአት ፍዳ መዳን  ፈጣሪውን እንዲያውቅ መሆን  ሐዲስ ተፈጥሮ  በቅድስና ማደግ ፩.፪. ነገረ ድኅነት በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ ነገረ ድኅነትም ሆነ ስለ ማናቸውም ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ለመረዳት ቅዱሳት መጻሕፍትን መመልከት አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ማናቸውም የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮዎች ዋና ማዕከላቸው እነዚህ መጻሕፍት በመሆናቸው እና ከእነዚህ መጻሕፍት ውጪ የሆኑ ማንኛውም አስተምህሮዎች ተቀባይነት ስለሌላቸው ነው። ከዚህ በተጨማሪ ስለ ሀይማኖታዊ ጉዳዮች ስናነሣ አንዲት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ብቻ መመርኮዝ የለብንም። አንዲቷን ጥቅስ ከአጠቃላዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ለይተንና ከሌሎች ጥቅሶች ነጥለን መመልከት የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ያደርሳል። ደካማ ሰው አንድን ጥቅስ ብቻ ነጥሎ በማንጠልጠል የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ሲደርስ ብልህ ፣ ጠቢብና ዕውቀት ፈላጊ ሰው ግን አንዱን ከአንዱ ጋር እያነጻጸረ በማጥናት ፣ በመታገሥ ምርምሩን ይቀጥላል፤ በዚህም ትክክለኛውን ዕውቀት ላይ ይደርሳል ፤ እውነትን ወደ ማወቅም ይመጣል። ከኦርቶዶክሳውያን አባቶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት በነገረ ድኅነት ውስጥ የሚከተሉትን ማንሳት እንችላለን።  ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ትምህርቱ የክርስቶስ መላ ሕይወት በሙሉ መዳንን ያስገኘልን መሆኑን በአጽንኦት ይገልጻል። መዳናችንን ክርስቶስ በሥጋዌው በመላ የፈጸመው የእርሱ የማዳን ሥራ ነው እንጂ በመስቀሉ ላይና በዕለተ ዐርብ ድርጊት ዙሪያ ላይ ብቻ የሚወሰን አይደለም። ለመዳናችን በአባቱ ዕቅፍ ከነበረበት ጀምሮ እስከ ልደቱ ፣ ስደቱ ፣ ጥምቀቱ ፣ መጾሙ ፣ ማስተማሩ ፣ ተአምራት ማድረጉ ፣ ስቅለቱ ፣ ሕማማቱ ፣ ትንሣኤው ፣ ዕርገቱ እና ዳግም ምጽአቱ ሁሉ እንጂ ዕለተ ዐርብና ስቅለቱ ብቻ አይደለም።  ማዳን ለክርስቶስ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን የአብና የመንፈስ ቅዱስም ሥራ ነው። የእኛ መዳን ክርስቶስ ሊፈጽመው የመጣው የሰማያዊ አባቱ ፈቃድ ነው።(ዮሐ ፬፥፴፬፣ ፭፥፴ ፣ ፮፥፴፷ ፤ ዕብ ፩፥፩ ፣ ፫፥፩᎐፮ ፣፭፥፬ ) እግዚአብሔር አብ በዚህ በመዳናችን መፈጸም ላይ ሕያው የሆነ ሚና አለው። (ሉቃ ፳፫፥፵፮ ፤ የሐዋ ፫፥፳፮ ፤ ዕብ ፲፫፥፳) የወልድ ተግባር ከሰማያት ወርዶ የሰውን ባህርይ ተዋሕዶ መዳናችንን መፈጸምና ወደ አባቱ መመለስ ነው። መንፈስ ቅዱስ አማኒው ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ይሆንና ይዋሐድ ዘንድ ይቀድሰውና ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት እንዲያድግ ይረዳው ዘንድ ከአማኒው ጋር ይኖራል። በኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ የተገኘው መቀደስ ከመዳን ሊለይ አይችልም። መንፈስ ቅዱስ በሰው ልጅ ላይ የኖረው ከክርስቶስ ዕርገት በኋላ ነው። ጌታችን “እኔ ባልሔድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና” እንዳል። ዮሐ ፲፮ ፥ ፯ ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ በአርስዮሳውያን ላይ በጻፈው ድርሳኑ “እኛ መንፈስ ቅዱስን እንቀበል ዘንድ ቃል ሥጋችንን ገንዘብ አደረገው። የክርስቶስን የማዳን ተግባር ለእያንዳንዳችን የሚፈጸመውና ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረትና ሱታፌ ይኖረው ዘንድ የሚያደርገው መንፈስ ቅዱስ ነው። ” ብሏል። ስለዚህ መዳናችን የእግዚአብሔር አብ ፣ የእግዚአብሔር ወልድ እና የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የአንድ አምላክ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድና ስጦታ ነው እንጂ የወልድ ብቻ ተደርጎ ተነጥሎ አይታይም። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ/ሰ/ት/ ቤቶች ማደራጃ መምሪያ 5 የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት መሠረተ ሀይማኖት ስምንተኛ ክፍል  መዳን ከኃጢአት ይቅርታ ባሻገር ብዙ ነገሮችን የያዘ ሰፊና ጥልቅ ነገር ነው። ስለዚህም አንደኛውንና የመጀመሪያውን ሥጦታ (የኃጢአት ይቅርታ ማግኘትን) ብቻ ሌላውን እስከሚያስረሳ ድረስ ማጉላትና ከዚያ ያለፈ ነገር የሌለ ማስመሰል እግዚአብሔር የሰጠውን ጸጋ ማሳነስና የተጠራበትን ከፍ ያለውን የእግዚአብሔር ጥሪ ማስረሳት ነው። በመጽሐፍ ቅዱሳዊና በአበው ቀደምት አስተምህሮ መሠረት መዳን ስንል ሥርየተ ኃጢአት ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን ማወቅን፣ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ማግኘትን ብርሃናዊነትን ገንዘብ ማድረግን፣ ከባርነት ነጻ መውጣትን፣ አዲስ ተፈጥሮንና የጸጋ አምላክነትን ገንዘብ ማድረግን ሁሉ የሚጨምር ሰፊና ጥልቅ ነው።  ሰው መዳንን ገንዘብ ማድረግ የሚችለው በኹለት ነገሮች ትብብር ነው። የመጀመሪያው እንደ ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት መዳን የጸጋ ሥጦታ መሆኑን መገንዘብ እና መሻት ይኖርበታል። ኹለተኛው ይህንን የጸጋ ሥጦታ ገንዘብ ለማድረግ የሚያስችል መታመን ወይንም እግዚአብሔር የሚወደውን ነገር ማድረግ እርሱ ከሚጠላው ነገር መራቅ ያስፈልገዋል። የጸጋው ሥጦታ እንዲሁ የሚሰጥ ቢሆንም የሰውን ነጻ ፈቃድ ወይንም ነጻነት ግን የሚጋፋ አይደለም። ለሰው ድኅነት የኹለቱ መኖር ወይም መስተጋብር የግድ አስፈላጊ መሆኑን በአጽንዖት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች። ከዚህ የምንረዳው መዳን በአንድ በኩል በሰው ጥረትና ችሎታ ያልተገኘ የእግዚአብሔር ጸጋ መሆኑን ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ሰው ያለ ራሱ ፈቃድና ሱታፌ እንዲሁ ከውጭ የሚጫንበት ግዴታ አለመሆኑን ነው። ፩.፫. የአዳም አወዳደቅ እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር ለሌሎች ፍጥረታት ያላድረገውን ልዩ ነገር በማድረግ ነው። ይኸውም ሰውን በመልካችን እንደምሳሌያችን እንፍጠር በማለት በራሱ መልክና ምሳሌ ፈጠረው። እንዲሁም ሰውን በሕያዊት ነፍስ አክብሮ ፣ ነጻነትን ሰጥቶ ፣ ክፉውንና በጎውን መለየትና መምረጥ የሚችል አዋቂና አስተዋይ አድርጎታል። ለዚህም ይረዳው ዘንድ ክፉ እውቀትን ወደ ማወቅ እንዳይሔድ የሚኖረው እውቀት ምን ጊዜም መልካም የሆነና የማይጎዳ ብቻ ይሆንለት ዘንድ “ከገነት ዛፍ ኹሉ ትበላለህ ነገር ግን መልካሙንና ክፉውን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና ” በማለት አዘዘው። ዘፍ ፪፥ ፲፮ - ፲፯ ይህ ሕግ የሰው ልጅ ለፈጣሪው ያለውን ፍቅር ይገልጽበት ፣ ታዛዥነቱን ያሳይበት ዘንድ የተሰጠው መንገድ ነበር። ነገር ግን የሰው ልጅ ይህንን ኹሉ ቸርነት ካደረገለት ከእግዚአብሔር ይልቅ ምንም ነገር ያላደረገለትንና ባዶ የሆነ የቃል ተስፋ ብቻ ይዞ የመጣውን እንደውም ለሞት የሚያበቃውን ዲያቢሎስን በማመን በፈጣሪው በእግዚአብሔር ላይ አመጸ ። በፈጣሪው ላይ ያለው እምነትና ፍቅር መገለጫ የነበረውን አትብላ የተባለውን ትዕዛዝ በማፍረስ ዕፅ በለስን በመብላት ሕገ እግዚአብሔርን አፍርሶ ትዕዛዙን ጥሶ የተሰጠውን ሕይወት ፣ ጸጋና ክብር በራሱ ጥፋት በማጣት ከሕይወት ወደ ሞት ፣ ከክብር ወደ ኃሳር ወረደ፤ የሞት ሞት ተፈረደበት ። የአዳም ዋነኛው ኃጢአቱ ቅጠል ቆርጦ መብላቱና አለመታዘዙ ሳይሆን እግዚአብሔርን አለማመኑ ነው። አለመታዘዙ የመጣው ካለማመኑ ነው፤ ይህም ማለት አዳምን የፈጣሪውን ትእዛዝ ወደ መጣስና ሕጉን ወደ ማፍረስ የወሰደው በእግዚአብሔር ላይ የነበረው እምነት በዲያቢሎስ ስብከት ከተለወጠ በኋላ ነበር። እግዚአብሔር ከመናገር በላይ የሆነ ብዙ መልካም ነገርን አድርጎለታል ፣ እንዲሁም ለራሱ ሲል ከዚህ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና እንዳትበላ በማለት አስጠንቅቆታል ሆኖም ግን እግዚአብሔርን በመጠራጠር ካደው። በአንጻሩ ደግሞ ምንም መልካም ነገር ያላደረገለትን ዲያቢሎስን አመነው። ዲያቢሎስ ሞትን እንደማይሞቱ ይልቁንም ቅጠሉን በበሉ ጊዜ እንደ እግዚአብሔር እንደሚሆኑ በመናገር እግዚአብሔርን ክፉ ራሱን ደግሞ አዛኝና ተቆርቋሪ አስመስሎ ሲሰብካቸው እግዚአብሔርን ተጠራጠሩት ዲያቢሎስን ግን አመኑት ። ዘፍ ፫፥፬ - ፭ አዳምና ሔዋን በእግዚአብሔር ላይ የነበራቸው እምነት ስለጠፋ ሕጉን በማፍረስ አለማመናቸውን በተግባር ገለጡ። የሀይማኖት ምልክት የሰው መታመን መግለጫ የነበረችውን ዛፍ ፍሬዋን ቆርጠው በሉ። ዲያቢሎስን ደግሞ በእርሱ ስብከት ላይ ያላቸውን እምነት የነገራቸውን በመፈጸም ለእርሱ በመታዘዝና እንዳስተማራቸው ፍሬዋን በመብላት በተግባር ገለጹ። በዚህ መልኩ የሰው ልጅ ከነበረበት የልዕልና የክብር ሕይወት ተዋርዶ ወደቀ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ/ሰ/ት/ ቤቶች ማደራጃ መምሪያ 6 የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት መሠረተ ሀይማኖት ስምንተኛ ክፍል ፩.፫.፩. አዳም ወደቀ ስንል ምን ማለታችን ነው? የሰው ልጅ ፈጣሪውን ማመን ትቶ ዲያቢሎስን ባመነ ጊዜና ፈጣሪውን መካዱንም የእምነት ምልክት የነበረችውን ዛፍ ቆርጦ በመብላት ከሐልዮ ወደ ገቢር በማሳደግ በተግባር ባረጋገጠ ጊዜ በዚያው ቅጽበት ከዚያ በፊት በባሕርዩ አብሮት ያልነበረ ነገር ግን በኃጢአቱ ምክንያት የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከእግዚአብሔር የመለየቱ ውጤት የሆኑ ብዙ ተደራራቢ ነገሮች ደርሰውበታል ። እነዚህም ፦  የሞት ፍርድ የሰው ልጅ ጥንቱን ሲፈጠር ለሞት ሳይሆን ለሕይወት ነበር። ይህ ስንል ግን ሰው ሲፈጠር እንደ መላእክት ከመጀመሪያውም የማይሞት ተደርጎ አልነበረም። ነገር ግን ሕጉን ቢጠብቅ በሕይወት ሊኖር ባይጠብቅ ደግሞ ሊሞት እንዲችል ሆኖ በማዕከላዊ ሁኔታ ተፈጥሯል። አዳም የተሰጠውን ሕገ እግዚአብሔር ቢጠብቅ ወደ ዘለዓለም ሕያውነት ተሸጋግሮ ሊኖር ባይጠብቅ ደግሞ ወደ ሞት ሊወርድ የሚችል ሆኖ በሙሉ ነጻነት የተፈጠረ ነበር። ሰው መሞት የሚችል ሆኖ መፈጠሩ የታዘዘውን ሳይጠብቅ ቢቀር በሕግ አፍራሽነቱ የሚደርስበት የባሕርይ መጎስቆል ዘለዓለማዊ አካል እንዳይሆንበት ነው። በበደለ ጊዜ በሰው ላይ ሞትን ማዘዙ በራሱ የእግዚአብሔር የቸርነቱ ሥራ ነበር። ይህም በኃጢአት ምክንያት ወደ ውስጣችን ዘልቆ የገባው የባሕርይ መጎስቆል በሞት ከእኛ ይወገዳል። በአንጻሩ ደግሞ እግዚአብሔር የፈጠረውና በሐዲስ ተፈጥሮ ያከበረው ሰውነታችን ደግሞ በትንሣኤ በክብር ይነሣል።  የባሕርይ መጎስቆል የሰው የባሕርይ ተፈጥሮ እጅግ ግሩም በሆነ ሁኔታ በክብር የተፈጠረ ነበር። ይህም እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥረው የብርሃን ልብስን አጎናጽፎ በአርዓያውና በምሳሌው ውብ አድርጎ ነበር የፈጠረው። ሆኖም ግን ሕጉን ሲያፈርስ የለበሰው የብርሃን ልብስ ተገፎ ራቁቱን ሆነ። አስቀድሞ የፍጥረታት ገዢ የነበረው የሰው ልጅ ክብሩን ሲያጣ ከርሱ ላነሱ ሥነ ፍጥረታት ተገዢ ሆነ። ለእግዚአብሔር ባለመታዘዙ ምክንያት ሰውነቱ ለራሱ አልገዛለት አለው። ይህም የሚፈልገውን መልካም ነገር ትቶ የማይፈልገውን ክፍ ነገር ወደ ማድረግ የሚሳብና የሚሸነፍ መሆኑን የሚያሳይ ነው።  ስደተኛ መሆን እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ፈጥሮ ርስት እንዲሆነው ገነትን ሰጥቶት ነበር። ነገር ግን ሰው የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በተላለፈ ጊዜ ከቦታው ከገነት ተባረረ፣ የራሱ ኃጢአት አሳድደው ። በዚህም ባለ ርስት የነበረው የሰው ልጅ በኃጢአቱ ከርስቱ ስለወጣ በስደተኝነቱ ያጣውን ርስት የሚናፍቅ የሚጠብቅ ሆነ። “እኔ በምድር ሳለሁ መጻተኛ ነኝና እንደ አባቶቼም እንግዳ ነኝ” መዝ ፵፯፥፰  ሰላም ማጣት የሰው ልጅ ኃጢአትን ሰርቶ የሰላም አምላክ ከሆነው ከእግዚአብሔር በመለየቱ ምክንያት የሚፈራ ፣ የሚደነግጥ ፣ የሚጨነቅ ፣ የሚታወክ ኾነ። ከመበደሉ በፊት የእግዚአብሔርን ድምጽ መስማት የደስታው ምንጭ የነበረ የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን ድምጽ ሲሰማ ሥራው ትዝ እያለው ይፈራና ይሸሽ ጀመር ። የራሱ ክፋትና ኃጢአት ሰላሙን አሳጣው። “ለክፉዎች ሰላም የላቸም ” ኢሳ ፵፰፥፳፪ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ/ሰ/ት/ ቤቶች ማደራጃ መምሪያ 7 የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት መሠረተ ሀይማኖት ስምንተኛ ክፍል  መንፈሳዊ እድገት መቋረጥ የሰው ልጅ ሲፈጠር በቅድስናና በጸጋ እያደገ መሔድ እንዲችል ነበር። ሆኖም ግን ከውድቀቱ በኋላ የነበረው እድገቱ ተቋረጠ መቋረጥ ብቻ ሳይሆን ጉዞው በተቃራኒ አቅጣጫ ኾነ። ይህም ሂደቱ ከመከራ ወደ መከራ ከውርደት ወደ ውርደት የሚመራው ኾነ። በዚህም ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት ወይንም ኅበረት ተቋረጠ። “የእግዚአብሔር መልክ (አርዓያ እግዚአብሔር) በተፈጥሮ ተሰጥቶናል ስለዚህም አይለወጥም ፤ ከመጀመሪያው ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ እንዳለ ይኖራል። ምሳሌውን (አምሳለ እግዚአብሔርን) የምናገኘውና የምንደርስበት ግን በራሳችን ፈቃደኝነትና ከእርሱ ጋር በሚኖረን የፈቃድ ኅብረትና ትብብር ነው። በእኛው ውስጥ የመኾን ክሂለ ከዊን አለ ፣ በመልካም ምግባር ሕይወትና በጥሩ የቅድስና ሕይወት ማደግና ወደ ታሰበው ግብ መድረስ እንችላለን።”( ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ) ስለዚህ የሰው ልጅ ውድቀት ስንል ከላይ የዘረዘርናቸው ነገሮች በሰው ባሕርይ ውስጥ መምጣታቸው ለእግዚአብሔር ባለመታዘዙ ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር መለያየቱን እንዲሁም ከእግዚአብሔር ጋር መለያየቱ ደግሞ እነዚህን ነገሮች እንዳመጡበት መገንዘብ አስፈላጊ ነው። ፩.፫.፩. ለአዳም መሳሳት ተጠያቂው ማን ነው ? የሰው ልጅ ለውድቀቱ ምክንያት ይሆነው ዘንድ የተለያዩ ነገሮችን ማቅረብ ይወዳል። ለሰው ልጅ ውድቀት የተለያዩ አካላትን ምክንያት ሲያደርጉና የሰው ልጅ ጥፋት የሌለበት መሆኑን አያይዘው ሲናገሩ ከተለያዩ አካላት ይሰማል። እንደ ምክንያት አድርገው ከሚያቀርቧቸው ነገሮች መካክል ዕጸ በለስ እና ዲያብሎስ ይገኙበታል። እንደ ቤተ ከርስቲያናችን አስተምህሮ ለአዳም ውድቀት ተጠያቂው እነዚህ አካላት አለመሆናቸውን ልብ ለማለት ያስችለን ዘንድ የሚከተሉትን ሐሳቦች እንመልከት።  ዕፀ በለስ ዕፀ በለስ እግዚአብሔር ከፈጠራቸው የዕፀዋት ፍጥረት መካከል ስትሆን ራስዋን ችላ ምንም ነገር ማድረግ አትችልም። ለምሳሌ ፦ በራሷ ወደ አዳም ተጉዛ ብላኝ አላለችም ፣ ዕፀ በለስ በራሷ መርዛማ አይደለችም። የመጀመሪያው ዕፀ በለስ የተፈጠረችበት ዓላማ የሰው ሀይማኖቱ ጽኑ እንዲሆን ነው። ይህም የሰው ልጅን እግዚአብሔር አልቆና አብልጦ ከፈጠረው በኋላ ፈጣሪው እርሱ መሆኑን እንዲያምን ካመነ በኋላ ደግሞ መታመኑን የታዘዘውን ትእዛዝ በመጠበቅ እንዲያረጋግጥ ለምልክት የተቀመጠች ናት። ኹለተኛው ዕፀ በለስ የተፈጠረችው እግዚአብሔር ለአዳም ያለውን ፍቅር ከኹሉ አልቆ በመፍጠር በመግቦት ስላሳየው እርሱ ደግሞ ለእግዚአብሐኢር ያለውን ፍቅር የፈጣሪውን ሕግና ትእዛዝ በማክበር እንዲያሳይ ነው። “ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው።” ዮሐ ፲፬፥፳፩ ይህ የሚያሳየን ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር የሚገለጠው ትእዛዙን በማክበር ውስጥ መሆኑን ነው። ሦስተኛ ዕፀ በለስ የተፈጠረችው የአዳም ፍጡርነት የእግዚአብሔር ፈጣሪነት እንዲታወቅ ነው። አስቀድሞ ዲያብሎስ ፍጡርነቱን ችላ በማለት እኔ ፈጥሬያችኋለሁ ብሎ በትዕቢት የክህደት ትምህርቱን ዘርቷል። ስለዚህ እግዚአብሔር ለአዳም ፍጡር መሆኑንና ፈጣሪ እንዳለው የምታሳውቅ ምልክት ሰጠው ። ሌላኛው ዕፀ በለስ የተፈጠረችው የአዳም ነጻ ፈቃዱ ይገለጥ ዘንድ ነው ። የአንድ ሰው ነጻ ፈቃዱ የሚታወቀው የመምረጥ መብት ሲኖረው መሆኑ የታወቀ ነው ያለበለዚያ ግን መመሪያ እንጂ ነጻ ፈቃድ አይሆንም ። አዳም ኹለት ምርጫ ተሰጥቶታል፤ ይህም የሚበላው እና እንዳይበላ የተሰጠው ትእዛዝ ነው። እንዲበላ ያልተፈቀደለትን ማለትም ዕፀ በለስን ካልበላ በሕይወት ይኖራል፤ ቢበላ ደግሞ የሞት ሞትን ይሞታል። በመሆኑም እጁን ወደ ፈቀደው መዘርጋት የሚችልበት ሥልጣን ወይም ነጻ ፈቃድ ተሰጥቶታል። በመሆኑም ዕፀ በለስ የተፈጠረችው በእነዚህ ምክንያቶች ስለሆነ በአዳም መውደቅ ውስጥ ዕፀ በለስ ተጠያቂ አይደለችም ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ/ሰ/ት/ ቤቶች ማደራጃ መምሪያ 8 የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት መሠረተ ሀይማኖት ስምንተኛ ክፍል  ዲያብሎስ ዲያብሎስ ራሱን ከክብር ያዋረደ ትዕቢትንና ሐሰትን ከራሱ አፍልቆ ራሱን ያጠፋ ነው። ታዲያ ዲያብሎስ እሱ ያጣውን ክብር እኛም እንድናጣ ፈልጎ ወደ ሔዋን መጥቶ ክፉ ምክርን መከራት ። እግዚአብሔርን እንዳታምን ውሸታም አድርጎ አቀረበላትና ዕፀ በለስን ቀጥፋ እንድትበላ አነሣሣት። አዳምና ሔዋን ኹለት ምክሮች ቀርበውላችው የነበረ ሲሆን የመጀመሪያው መልካም ምክር የእግዚአብሔር ምክር ነበር። ኹለተኛው ምክር ደግሞ የእግዚአብሔርን ምክር የሚያፈርስ የዲያብሎስ ክፉ ምክር ነው። ከዚህ በኋላ አዳምና ሔዋን ወደውና ፈቅደው ከእግዚአብሔር መልካም ምክር ወይንም ትእዛዝ የተሻለ ነው ብለው የእግዚአብሔርን ሕግ ጥሰው በዲያብሎስ ትእዛዝ ተመርተው ዕፀ በለስን በሉ። ዲያብሎስ እጃቸውን ይዞ አላስቆረጣቸውም ወይንም ቆርጦ አላጎረሳቸውም። የዲያብሎስ ድርሻ የነበረው ምክር ማቅረብ ነበር ። ምክንያቱም ስህተት እንድናደርግ የማስገደድ መብት ስለሌለው ነው። “ለእግዚአብሔር ተገዙ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል ። ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል። ” ያዕ ፬፥፰ ሆኖም ግን ዲያብሎስን የሚቃወሙበት ብዙ ነገሮች እንዲሁም ሥልጣኑም ነበራቸው። እነርሱ ግን እግዚአብሔር ካደረገላቸው ብዙ መልካም ነገሮች በመዘናጋት መብታቸውንና ሥልጣናቸውን አሳልፈው ሰጡት ። በመሆኑም ለአዳምና ሔዋን መሳሳት ዲያብሎስ ተጠያቂ አይደለም ። ስለሆነም ምንም ያህል ሰዎች ለውድቀታቸው ምክንያትን የሚሹ ኾነው ቢገኙም ምክንያት ብለው ያቀረቡትም ነገር ቢኖር እውነታው ግን ለሰው ልጅ ውድቀት ተጠያቂው ራሱ የሰው ልጅ ነው። ለነጻነት ተብሎ በተሰጠው ጸጋ ተጠቅሞ መንግሥቱን መውረስ ሲችል በምክረ ከይሲ ተታሎ መንግሥቱን አጣ፤ የዲያብሎስ ባርያ ኾነ ። ይህ ሁሉ ነገር ቢሆንም ግን በንስሓ ተመልሶ የሚድንበትን መንገድ የሚያድነውን አካል በተስፋ ይጠባበቅ ነበር። የምዕራፍ ፩ ማጠቃለያ ጥያቄዎች፤ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ትክክል ከሆኑ እውነት ስህተት ከሆኑ ደግሞ ሐሰት በማለት መልስ ስጡ፡፡ ፩ በነገረ ድኅነት መዳን ስንል የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ በማፍረሱ ምክንያት ከደረሰበት የባሕርይ መጎስቆል በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተደረገለትን ድኅነት ማለታችን ነው። ፪ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር በመለየቱ ምክንያት በቅድስና ማደግ ተስኖት በተቃራኒው ይጓዝ ነበር ። ፫ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት የነገረ ድኅነት ዋና ማዕከል ቅዱሳት መጻሕፍት ናቸው። ፬ የሰው ልጅ የተፈጠረው በእግዚአብሔር አርዓያ እና አምሳል ነው። ፭ ዕፀ በለስን እግዚአብሔር የፈጠረው የሰውን ልጅ ለሰው ልጅ ነጻ ፈቃድ ለመስጠት ነው ። ለሚከተሉትን ጥያቄዎች ትክክለኛውን መልስ ስጡ ። ፮ ለሰው ልጅ በኃጢአት መውደቅ ተጠያቂው ማን ነው ? ፯ ነገረ ድኅነት ማለት ምን ማለት ነው ? የቃሉን ፍቺ በማብራራት ግልጹ ። ፰ በነገረ ድኅነት አስተምህሮ መሠረት የሰው ልጅ ወደቀ ስንል ምን ማለታችን ነው ? ፱ በሰው ልጅ ውድቀት ውስጥ የባሕርይ መጎስቆል ማለት ምን ማለት ነው ? ፲ ስለ ነገረ ድኅነት ከአበው አስተምህሮዎች መካከል በመጥቀስ አብራርታችሁ ጻፉ ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ/ሰ/ት/ ቤቶች ማደራጃ መምሪያ 9 የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት መሠረተ ሀይማኖት ስምንተኛ ክፍል ምዕራፍ ኹለት ዓላማ ተማሪዎች ይህንን ምዕራፍ ተምረው ሲያጠናቅቁ ፦ ፩ የሰው ልጅ በኃጢአት ምክንያት ከመጣበት ውድቀት ያዳነው ማን እንደሆነ ይረዳሉ። ፪ የሰው ልጅ የዳነው ከምን እንደሆነ ተረድተው ያብራራሉ። ፫ በነገረ ድኅነት ውስጥ የሰው ልጅ ድርሻ ምን እንደሆነ ይገነዘባሉ ? ፬ በነገረ ድኅነት ውስጥ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሱታፌ (ድርሻ) ምን እንደሆነ ይገነዘባሉ። የማስጀመሪያ ጥያቄ ፩ የሰውን ልጅ ከተፈረደበት የዘላለም ሞት ያዳነው ማን ነው ? ፪ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት ውስጥ ያላት ድርሻ ምንድነው ? ፫ በነገረ ድኅነት ውስጥ የሰው ልጅ ድርሻ ምንድነው ? ፪. ፪.፩. ያዳነን ማን ነው? የሰው ልጅ ከሞት ወደ ሕይወት የሚያሸጋግረው፣ ከባርነት ወደ ነጻነት የሚያወጣው ፣ መድኃኒት የሚሆንለት ፣ ያጣውን ሰላም የሚመልስለት እና ወደ ባሕርዩ ውስጥ ዘልቆ የገባውን ሞት የሚያስወግድለት ያስፈልገው ነበር ። ስለሆነም ሰውን ያዳነው ወደ ራሱ ያቀረበው ልዑለ ባሕርይ ቅዱስ እግዚአብሔር ስለመሆኑ መላዕክትም ሆኑ ነቢያት የሰውን ልጅ ለምን ማዳን እንዳልቻሉ እንመለከታለን።  ነቢያት የሰውን ልጅ ማዳን ስለምን አልተቻላቸውም ? ነቢያት ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ሰዎች እየተላኩ ሕዝቡ ከኃጢአታቸው በንስሐ እንዲመለሱና በበደላቸው ምክንያት ከሚመጣባቸው ቁጣ እንዲድኑ የሚያስተምሩና የሚመክሩ ናቸው። እነዚህ ነቢያት እግዚአብሔር ወደ ሚልካቸው ቦታዎች እና ነገሥታት ጋር በመሔድ ያለ ፍርሐት እውነቱን የሚናገሩ በመሆናቸው ብዙ መከራና ሥቃይ ዓላውያን ከሆኑ ነገሥታት ደርሶባቸዋል። ሆኖም ግን ይህ ኹሉ የሚቀበሉት መከራና ሥቃይ አዳምና ሔዋን ላይ ከመጣው ውድቀት፣ ከሞትና ከእግዚአብሔር መለየት ሊያድን አልቻለም። እንደውም በተቃራኒው ነቢያት በአዳምና በሔዋን የተፈረደው የሞት ፍርድ ጽዋ ቀማሾች ስለነበሩ ለእነርሱም የሚያድናቸውን ባለ መድኃኒት የሚሹ ነበሩ። “ሁላችን እንደ ርኲስ ሰው ኾነናል፥ ጽድቃችንም ኹሉ እንደመርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፥ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል።” ኢሳ ፷፬፥፮ ፤ መዝ ፸፱፥፩-፯ ፤ መዝ ፻፵፫፥፭-፰ የነቢያት ዋና አገልግሎት እና የትንቢታቸውም ትኩረት የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ መድኃኒት ቶሎ እንዲመጣ እና ድኅነት እንዲያደረግ ወደ እግዚአብሔር አጥብቀው መጸለይ እና ሕዝቡን ማጽናናት በክፉ ሥራ እንዳይጎዳ ማስተማርና መገሰጽ የእግዚአብሔርንም መንገድ ማሳየት ነው። ኢሳ ፵፥፩-፭ ነቢያት የበደለው የአዳም ልጆች ስለሆኑ በተጨማሪም ፍጡራን በመሆናቸው የሰውን ልጅ ከተፈረደበት የዘላለም ሞት ማዳን አይችሉም ። “ለእናንተም ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ መዳን ተግተው እየፈለጉ መረመሩት በእርሱም የነበረ የክርስቶስ መንፈስ ስለ ክርስቶስ መከራ ከእርሱም በኋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ እየመሰከረ በምን ወይም እንዴት ባለ ዘመን እንዳመለከተ ይመረምሩ ነበር። ለእርሱም ከሰማይ በተላከ በመንፈስ ቅዱስ ወንጌልን የሰበኩላችሁ ሰዎች አሁን ባወሩላችሁ ነገር እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳላገለገሉ ተገለጠላቸው ፤ ይህንም ነገር መላዕክቱ ሊመለከቱ ይመኛሉ።” (፩ጴጥ ፩፥፲-፲፪) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ/ሰ/ት/ ቤቶች ማደራጃ መምሪያ 10 የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት መሠረተ ሀይማኖት ስምንተኛ ክፍል  መላዕክት የሰውን ልጅ ማዳን ለምን አልተቻላቸውም ? መላዕክት ሰውን የሚራዱና የሚጠብቁ ፣ የእግዚአብሔርን ምሕረት ወደ ሰዎች የሰዎችን ልመና (ጸሎት) ወደ እግዚአብሔር የሚያሳርጉ ናቸው። “ኹሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?” ዕብ ፩፥፲፬ መላዕክት ሰዎች ከኃጢአት ወደ ጽድቅ በንስሐ ሲመለሱ ታላቅ ደስታን የሚያደርጉ የአንዲቷ ሀይማኖት አካላት ሲሆኑ ለሰዎች ልጆች በሀይማኖት መንገድ በማገዝና በመራዳት የሚያገለግሉ ናቸው። የበደለ ሰው በመሆኑ መላዕክት የሰውን ልጅ ከወደቀበት ውድቀት ሊያድኑት አልተቻላቸውም ። በተጨማሪም መላዕክት ፍጡራን ስለሆኑ የፈረሰውን የእግዚአብሔርን ቃል ያስከተለውን ጉዳት መመለስ አልቻሉም። ይህም የሚያሳየን የሰው ልጅ ድኅነት ከፍጡራን አቅም በላይ መሆኑን ነው።  መሥዋዕተ ኦሪት ስለምን የሰውን ልጅ ማዳን አልቻለም ? መሥዋዕተ ኦሪት ትክክለኛው መድኃኒት እስከሚመጣ ድረስ ማቆያና ምሳሌ ሆነው የሚያገለግሉ ነበሩ። እነዚህ መሥዋዕት የሚሰውት የሰው ልጆች ላይ ከሚመጣው ሥጋዊ መቅሰፍት ለመዳን እንጂ መንፈሳዊ ድኅነትን ለመስጠት አይደለም። ዋናው የሕገ ኦሪት አገልግሎት ለሕገ ወንጌል የትንቢትና የተምሳሌት ምስክርና ማስረጃ መሆን ነበር። ስለሆነም ይህ የኦሪት መሥዋዕት የሰውን ልጅ የሚያድን ፣ ሞቱን የሚያጠፋለት ፣ ሕይወትን የሚያጎናጽፈው ፤ ሰላምን የሚሰጠው እና ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ሕብረት አንድነት የሚመልስለት አይደለም።  እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ያዳነው እንዴት ነው ? ከላይ የዘረዘርናቸው ፍጥረታትም ሆኑ የተሰዉ መሥዋዕቶች የሰውን ልጅ ከተፈረደበት ፍርድ ከደረሰበት ውድቀት ማዳን ስላልቻሉ (ስለማይችሉ) የሰው ልጅን ለማዳን እግዚአብሔር ፈቃዱ ኾነ። እግዚአብሔር አምላክ አዳምን በዕለተ ዐርብ ከኹሉ ፍጥረታት አልቆና አብልጦ ለክብር በአርዓያውና በአምሳሉ ፈጥሮታል። ኋላም አታድርግ ያለውን ባደረገና በንስሓ በተመለሰ ጊዜ የሚድንበትን የተስፋ ቃል ሰጥቶታል። ስለሆነም በሰው ልጅ ላይ የደረሰውን ጥፋት በኃይሉ ማጥፋት የሚቻለው ራሱ እግዚአብሔር ብቻ ስለሆነ በፍርዱ ፈታሒነቱ ይታወቅ ዘንድ እርሱን ለማዳን ሰው ሆነ። የሰው ልጅ በደል የሚያጠፋለት እግዚአብሔር የሚከተሉትን ነገሮች ኾኖለታል።  ሰው ኾኗል ፦ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ለማዳን ሰው መሆን አስፈልጎታል ምክንያቱም የበደለውና የተፈረደበት የሰው ልጅ ነው። የበደለው ሰው ኾኖ ሳለ ሌላው በርሱ ፈንታ ገብቶ ቢያድነው ችግሩና መፍትሔው በትክክል አይገጣጠሙም ፤ ሙሉም አይሆንም ነበር። ስለዚህ ለበደለው የሰው ልጅ ዋጋ ለመክፈል እግዚአብሔር ሰው ኾኗል። “ቃል የእኛን ባሕርይ የተዋሐደውና ሰው የኾነው ሰዎች የጸጋ አማልክት ይኾኑ ዘንድ ነው። ”( ቅዱስ ሄሬኔዎስ) ተግባር  ተማሪዎች እግዚአብሔር አምላክ ሰው ኾነ ስንል ምን ማለታችን ነው ? ሰው የኾነውስ እንዴት ነው ? “ስለዚህ በመጀመሪያ ሰው ሆኖ ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር የሆነ አይደለም፤ እግዚአብሔር የነበረ ሲሆን ሰው የሆነ ነው እንጂ ፤ ይህም እኛን የጸጋ አምላክ አድርጎ ለማክበር ነው። ”( ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ትምህርት በእንተ አርዮሳውያን ትምህርት ፪፥፴፱) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ/ሰ/ት/ ቤቶች ማደራጃ መምሪያ 11 የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት መሠረተ ሀይማኖት ስምንተኛ ክፍል  በእርሱ ፋንታ ሞቶለታል ፦ የበደለው የሰው ልጅ ላይ የተፈረደበት ፍርድ ሞት ነው። ይህ ዕዳ ካልተከፈለ ደግሞ ሰው ነጻ ኾኖ ዳነ ለማለት የማይቻል ስለሆነና ፍርዱ ሳይፈጸም ቢድን ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል ተፈጻሚነት ላይ ጥያቄ የሚያስነሣ በመሆኑ እርሱን የሚያድነው አዳኝ መሞቱ የግድ አስፈላጊ ነበር። ስለዚህ እርሱን ለማዳን እግዚአብሔር ሰው ኾኖ በፈቃዱ የእርሱን ሞት ሞቶለታል። “በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ ፣ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና” ፩ዮሐ ፬፥፱  ሞትን በኀይሉ ድል አድርጎ ተነሥቷል ፦ የሰው ልጅ ላይ የተፈረደውን የሞት ፍርድ ለማጥፋት ሰው መሆንና የተፈረደበትን የሞት ፍርድ እርሱ ተቀብሎ መሞቱ ብቻ ሊያድነው አይችልም ። መሞቱ የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱም የግድ አስፈላጊ ነበር። ስለዚህ የሰውን ልጅ ሊያድነው የሚችለው ሞቶ ሞትን አሸንፎ ወደ ሕይወት ጎዳና የሰውን ልጅ መውሰድ ሲችል ብቻ ነበር። ስለሆነም እግዚአብሔር ሰው ኾኖ በፈቃዱ ሞቶ እና ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቶ አድኖታል ።  ንጹሐ ባሕርይ መሆን አለበት ፦ ነቢያት የሰውን ልጅ ማዳን ያልተቻላቸው ከኃጢአት ውርስ ነጻ ያልሆኑ እና ንጽሕና የጎደላቸው በመሆናቸው ነው። ታዲያ ሰውን የሚያድነው ከበደልና ከኃጢአት ዕዳ ንጹሕ መሆን ይኖርበታል። ራሱ ንጹሕ ካልሆነ የሰውን ልጅ ለማዳን ቤዛ ለመሆን ቀርቶ ራሱም በበደሉ ምክንያት ማዳን ባልተቻለው ነበር ። ስለዚህ ንጹሐ ባህርይ መሆኑ የግድ አስፈላጊ ስለነበርና ሰው ኾኖ ከኃጢአት በቀር የሰውን ኹሉ ሥራ እየሠራ ቆይቶ መሥዋዕት ኾኖ አድኖታል። ዮሐ ፩፥ ፳፱ “ከኢፍጹምነት ወደ ፍጹምነት ለማደግ የጌታችን ሥጋዌ መሠረታዊ ነው። በጌታችን የማዳን ሥራ ከመልክአ እግዚአብሔር ወደ አርዓያ እግዚአብሔር ለማደግ የሚያስችለንና የሚያስፈልገን የነበረው ዓቅምና ችሎታ ተመለሰልን” (ቅዱስ ሄሬኔዎስ በእንተ መናፍቃን መጽሐፍ ፫ ምዕ ፲፰) ከላይ ካየናቸው ውስጥ ኹለቱ ማለትም ሰው መሆንና መሞት መቻል ሰዋዊ ባሕርይን የሚገልጡ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ኹለቱ ሞትን ማሸነፍ እና ንጽሐ ባሕርይ መሆን ደግሞ አምላካዊ ባሕርይን የሚገልጡ ናቸው። ሰው ብቻውን መሞት ቢችልም ሞትን ማጥፋትና ሞትን ድል ማድረግ ስለማይችል ኹለቱንም በአንድ በኩል ስለ ሰው ሲል ሰው መሆንን እና ሞትን በፈቃዱ መቀበልን በሌላ በኩል ሞትን ማሸነፍንና በንጹሕ ባሕርይነቱ ቤዛ መሆንን ማሟላት የሚቻለው እግዚአብሔር ስለሆነ ራሱ መድኃኒት ኾኗል። እግዚአብሔር በባሕርዩ ሞት የማይስማማው ቢሆንም ስለእኛ ድኅነት ሲል የእኛን ባሕርይ ገንዘብ ማድረግ አስፈለገው። “በመሞት ካልሆነ በቀር የሰው ሞት ሊወገድ እንደማይችል እግዚአብሔር ቃል ባየ ጊዜ እርሱ በባሕርዩ የማይሞት ስለሆነ ስለ ሁሉም መሞት ይችል ዘንድ የሚሞት የእኛን ባሕርይ ተዋሐደ ። ይህም የእኛ ባሕርይ ከተዋሐደው ከእግዚአብሔር ቃል የተነሣ የማይሞት ይሆን ዘንድ መሞትና መበስበስም በትንሣኤ ይጠፋ ዘንድ ነው። ቃል የተዋሐደውንና ገንዘቡ ያደረገውን ሥጋ ከበደል ንጹሕ የኾነ መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብና ለሞት በመስጠት ሞትን ከወገኖቹ አስወገደ። የሞትን ዕዳ ሞትን በመክፈል ከእኛ አስወገደው። ሞትና ጥፋቱ የእኛን ሥጋ ከተዋሐደው ከአካላዊ ቃል የተነሣ ሊገዛና ሊይዝ አልተቻለውም ። የኹሉ ጌታ መድኃኒት መጥቶ ሞትን ድል ባያደርገው ኖሮ የሰው ዘር ጠፊ ነበር ።”(ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ በእንተ ተሠግዎቱ ለቃል፤ ቁ.፱) እግዚአብሔር አምላክ ለአዳምና ለሔዋን አስቀድሞ በሰጣቸው የተስፋ ቃል መሠረት እርሱ ባወቀው ምሥጢር ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ ከንጽሕት ድንግል ቅድስት ማርያም ሰው ኾኖ ተወልዶ አድኖናል። የሰውን ልጅ ያዳነው ከወደቀበትም ውድቀት ሊያድነው የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ስለመኾኑ በቅዱስ መጽሕፍ በግልጽ ተቀምጦ እናገኘዋለን ። “በመልዕክተኛ አይደለም፣ በአማላጅም አይደለም ፣ እርሱ ራሱ ይመጣል ያድናቸውማል እንጂ” (ኢሳ ፷፫፥ ፱–፲) አምላካችን እግዚአብሔር እንዲህ ባለ ሁኔታ ራሱ መድኃኒት መሆኑን ነግሮናል ። ፍጡር ፍጡርን በተለያየ ሁኔታ እንደ አቅሙ ሊያግዘው ሊረዳው የሚችል ቢሆንም ነገር ግን በሰው ልጅ ላይ የደረሰውን ሞት አስወግዶ ሕይወትን ሊሰጠው የጎሰቆለ ባሕርዩን ያጣውን ጸጋ ሊመልስለት ግን አይችልም ። ይህንን ማድረግ የሚችለው ራሱ እግዚአብሔር ብቻ ነበር። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ/ሰ/ት/ ቤቶች ማደራጃ መምሪያ 12 የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት መሠረተ ሀይማኖት ስምንተኛ ክፍል “ተዋርዶ ለነበረው ለሰው ባሕርዩ ከእግዚአብሔር ጋር በምሥጢረ ተዋሕዶ ከመዋሐድና አንድ ከመሆን በላይና በዚህ ተዋሕዶም የጸጋ አምላክ ከመሆን በላይ ምን ክብርና ፍጻሜ ሊኖረው ይችል ነበር ?... ይህን ያደረገልንስ ስለ እኛ ራሱን ካዋረደውና ክብር የሌለው ሆኖ ከተገለጠው ነገር ግን በአምላክነቱ ባሕርይ ጉልበት ሁሉ ሊንበረከክለት የሚገባው ከሆነው ከራሱ ከእግዚአብሔር በቀር ማን ነው ?” ( ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ ነገረ መለኮታዊ ትምህርቶች ፥ ትምህርት ቁ.30) እግዚአብሔር ሰው የሆነው እና ሞትን ስለ ሰው ልጆች በፈቃዱ የተቀበለው የእግዚአብሔር ዓላማው የሰው ልጅ ድኅነት በመሆኑ ነው። የነቢያት ትንቢታቸው ዋና ማዕከል የሰው መዳን ነበር ። የሐዋርያት ተልእኮና ስብከት ዓላማው የሰው ድኅነት ነው። “እንግዲህ ሒዱና አሕዛብን ኹሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ኹሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” ማቴ ፳፰፥፲፱-፳ ቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉት ለሰዎች የመዳን እውቀትን ለመስጠት ነው። “ከሕጻንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉ ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል።” ፩ጢሞ ፫፥፲፭ ስለሆነም ከላይ የተመለከትናቸውን ነገሮች ኹሉ በማድረግ እግዚአብሔር የሰው ልጆችን አድኗቸዋል። ፪.፪. ሰው የዳነው ከምንድነው ? ፩ ከኃጢአት ፍዳ መዳን :- ይህ የሰው ልጅ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዙ ምክንያት የደረሰበት ቅጣት ነው። ቅዱስ እግዚአብሔር የሰውን ልጅን መጸጸት እና ንስሐ ተመልክቶ ከኃጢአት ፍዳ ለማዳን ሰው ሆኗል ። ሰው ሆኖም የኃጢአት ፍዳ የሆነውን ሞት እርሱ ራሱ በመስቀል ላይ ሞቶ ሞቱን ገደለለት፤ ያጣውን ሕይወት መለሰለት ። በባሕርዩ መጎስቆል ያጣውን ልጅነት መልሶለት ዳግሞኛ ልጅ የሚሆንበትን ረቂቅ ልደት ሰጠው፤ ይህ ከኃጢአት ፍዳ መዳን ይባላል ። ጌታችን እኛ ከሞትና ከርግመት እንድን ዘንድ ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ “ክርስቶስም ደግሞ እንደ ወደዳችሁ ለእግዚአብሔርም የመዓዛ ሽታ የሚሆንን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ ስለ እናንተ ራሱን አሳልፎ ሰጠ “ ኤፌ ፭፥፪ ክርስቶስ የመጣው ከኃጢአት ብቻ ሳይሆን ከሞትም ሊያድነን ነው። በሞት የደረሰብንን የነፍስና የሥጋ መለያየት ያድን ዘንድ ሥጋችንንና ነፍሳችንን ተዋሐደ ። ስለዚህም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሱና ሥጋው በሞት ጊዜ እንዲለያዩ ፈቀደ። ሆኖም መለኮት ከኹለቱም ጋር ማለትም ከሥጋውና ከነፍሱ ጋር የተዋሐደ ስለሆነና ስለማይለይ ሞት ሥጋውንም ሆነ ነፍሱን ይይዛቸው ዘንድ አልቻለም። ምክንያቱም የመለኮት መዋሐድ ከሥጋና ከነፍስ ጋር በመሆኑ ነው። ከሦስት ቀን በኋላም ቅድስት ነፍሱንና ክቡር ሥጋውን በትንሣኤ እንደገና አዋሕዷቸዋልና ሞትን በኀይሉ አጠፋው። የሰው ልጅ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ ተብሎ አስቀድሞ ተነግሮት የነበረው የሞት ማስጠንቀቂያ በገቢር ተፈጽሞበት በሰውነቱ ላይ ሞት ነግሦበት የሞት ተገዢ ሆኖ ነበር። ዘፍ.፪፥፲፯ በሕይወተ ሥጋ እያለም ኑሮው በጽላሎተ ሞት (በሞት ጥላ ሥር ) ውስጥ የወደቀና በሞት ስጋትና ፍርሃት የታጠረ ፣ ሲሞትም ነፍሱ በጻዕር ተለይታ ሥጋው ወደ መቃብር ነፍሱ ወደ ሲዖል በመውረድ በጭንቅና በመከራ ይኖር ነበር። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የሚስማማውን የእኛን ሥጋ በመዋሐድ ሞታችንን ሞቶ በሞቱ ሞትን አጠፋልን፣የእርሱን ሕይወት ለእኛ ሰጠን ሞትን በትንሣኤ ለወጠልን። የመቃብርን ይዞ የማስቀረትና ሰውነታችንን የማፍረስ ፣ የመለወጥ ኃይል ድል በማድረግ በመቃብር ተይዞ ፈርሶ በስብሶ መቅረትን አጠፋልን። በጌታችን ሞት ሞት ድል ኾነ ሲዖል ተመዘበረ ፣ መቃብር ተከፈተ ፤ ለዚህም ምስክሮችና በኩራት ይሆኑ ዘንድ በኢየሩሳሌም ሞተው ተቀብረው ከነበሩት ቀደምት ወገኖች መካከል የተወሰኑትን ከመቃብር በማንሣት ለሰዎች እንዲታዩ አደረጋቸው ። “ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ” ማቴ ፳፯፥፶፫ ፪ ፈጣሪውን ካለማወቅ ፦ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ኅበረት ከተለየ በኋላ የፈጠረውን ፈጣሪውን ኹሉ እስከመርሳት ደርሷል። የሰው ልጅ እንዲገለገልበት ለተፈጠሩት ፈጥረታት ሲያጎነብስና እነርሱን አምላክ አድርጎ ሲያመልካቸው ቆይቷል። ሌላው ቀርቶ መናፍስትን እንኳን ሳይቀር ፈጣሪ በማድረግ በሐሳት ጎዳና ሲጓዝ ኖሯል። ይህ ሁሉ የሆነው የሰው ልጅ ፈጣሪውን በመዘንጋቱ ወይንም ባለማወቁ የተነሣ ነው። እግዚአብሔር የሰውን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ/ሰ/ት/ ቤቶች ማደራጃ መምሪያ 13 የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት መሠረተ ሀይማኖት ስምንተኛ ክፍል ልጅ ያዳነው ፈጣሪውን ረስቶ በሐሰት ጎዳ ከመጓዝም ጭምር ነው። ይህም የእግዚአብሔር የቸርነቱ ማሳያ ነው። “ዓለም በጥበቧ እግዚአብሔርን ስላላወቀች በስብከት በሞኝነት የሚምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃዱ ኾኗልና። ”( ፩ ቆሮ ፩፥፳፩) ፫ ከጎሰቆለው ተፈጥሮ ፦ የሰው ልጅ በዲያብሎስ ተታሎ ተሸንፎ በመውደቁ ምክንያት ባሕርዩ ጎስቁሎ ነበር ። ጌታችን መድኃኒታችን ወደዚች ምድር መጥቶ ማስተማሩ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር መመላለሱ ይህንን የጎሰቆለውና ድል የተነሣውን ማንነት አስወግዶ በዐዲስ ማንነት ያትመን ዘንድ ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነው የኃጢአታችንን ዋጋ ለመክፈል ብቻ ቢሆን ኖሮ ያን ያህል ጊዜ ተዘዋውሮ ማስተማር ሳያስፈልገው ሞቶ ተነሥቶ ያድነው ነበር። ነገር ግን ይህ የሞተው የጎሰቆለው ባሕርይ ይወገድ ዘንድ አስፈላጊ ስለነበር ጌታችን በሐዲስ ተፈጥሮ የምንኖርበትን ማንነት ሰጥቶ አድኖናል። “ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን ዐዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፏል፤ እነኾ ኹሉም ዐዲስ ሆኗል” (ሮሜ ፮ ፥፬) ፬ ስደተኛ ከመሆን :- የሰው ልጅ ከቦታው ከገነት ተባረረ ፣ የራሱ ኃጢአት አሳደደው ። ቀድሞ የደስታው ምንጭ የነበረው የእግዚአብሔር ድምጽ አሁን ግን በሠራው ኃጢአት ምክንያት ያስፈራው ጀመር ። ስለዚህም ከእግዚአብሔር ሸሸ ፣ ለመሸሸግም ሞከረ ። እግዚአብሔር “ወዴት ነህ?” ብሎ በጠራውና በፈለገው ጊዜ “በገነት ድምጽህን ሰማሁ ፣ ራቁቴንም ስለሆንሁ ፈራሁ ፣ ተሸሸግሁም” በማለት እጅግ አሳዛኝ በኾነ ሁኔታ መለሰ። ዘፍ.፫፥፱-፲ እግዚአብሔርም የበደለውን አዳምን ቀኖና በመስጠት ከገነት አስወጣው “እግዚአብሔር አምላክ ከኤደን ገነት አስወጣው ፤ የተገኘባትን መሬት ያርስ ዘንድ አዳምንም አስወጣው ። ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በዔደን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ።”ዘፍ.፫፥፪፥፳ ስለዚህም ግዞተኛ ኾኖ ወደ ምድር ተጣለ። በመኾኑም እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ወደዚህ ምድር መጥቶ በከፈለው ዋጋ ዳግመኛ ባለርስት በመሆን ከስደተኝነት ለመዳን ችሏል። ፭ ከቅድስና ውጪ ከመሆን ፦ ከላይ ከተመለከትናቸው ሐሳቦች በመቀጠል የመዳን ቁልፍ ጉዳይ ይህ የቅድስና እድገት ነው። ይህ እድገት ከኃጢአት ቅጣት ነጻ ከመሆን በላይ የሆነ ድኅነት ሲሆን እግዚአብሔርን መምሰልን ገንዘብ ወደ ማድረግ የሚደረግ የማይቋረጥ ጉዞ ነው። ይህም ጉዞ ሱታፌ አምላካዊ በመባል ይታወቃ። መንፈሳዊነት ማለት ከእግዚአብሔር ጋር በመኖር የሚገኘውን ሕይወት ገንዘብ ማድረግ ሲሆን የእግዚአብሔር የባሕርያቱ መገለጫዎች የሆኑትንና ለሰው በፍጥረት ጊዜ የተሰጡትን ጸጋዎች ገንዘብ ማድረግና ወደ ፍጹምነት ማሳደግ ነው። በመሆኑም በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ ይህ የተቋረጠው እድገት ድጋሚ ለመቀጥል እድል ፈጥሯል። ፪.፫. በነገረ ድኅነት ውስጥ የሰው ልጅ ድርሻ የሰው ልጅ በምክረ ከይሲ ተታሎ ከነበረበት ልዕልና ተዋርዶ የኃጢአት ተገዢ ኾኖ በሞተ ሥራ ሲለይ በነፍስ ወደ ሲኦል ወርዷል። በሲኦል ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ከኖረ በኋላ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ፍቅርና የጸጋ ማዳን በጥፋቱ ከተባረረበት ርስቱ ካጣው ልጅነቱ እንዲመለስ ኾኗል። የታመሙት ድነዋል ፣ ሲዖል የነበሩት ወጥተዋል፡፡ ካሣው ለዂሉም ተከፍሏል፤ አምላካችን የሞቱትን አድኗል። በሕይወተ ሥጋ ያለን እኛ ግን ድኅነቱን ተቀብለን በሃይማኖት (በእምነት)፣ በጥምቀት፣ ቅዱስ ሥጋውን በመብላት፣ ክቡር ደሙን በመጠጣት የተሠራውን ሕግ በመጠበቅ ድኅነትን እናገኛለን። በዚህ የምንድን ሲሆን በሕጉ ካልኖርን ደግሞ እንቀጣለን፡፡ ስለዚህ ክርስትና ወይም ሕገ ወንጌል የዳኑትን (ክርስቶስ ከሲዖል በሞቱና በትንሣኤው ያወጣቸውን ) ለማዳን የተሰጠ ሕግ ሳይኾን ያልዳኑት (ድኅነቱ የተሰጣቸው) እንዲድኑ የተሰጠ ሕግ ነው፡፡ የኦሪት ሕግ (የኦሪት መሥዋዕት) ማዳን የሚችል አልነበረም ፤ ወንጌል ግን ለዓለም ድኅነት የተሰጠ ሕግ ነው፡፡ ሐዋርያት ዓለም እንዲድን የሕይወትን ወንጌል ይዘው ዞሩ፤ አስተማሩ፡፡ ወንጌል የተሰበከው ለዳኑት ሳይኾን ለሚድኑት ነው። የሰው ልጅ ለመዳን የሚስፈልጉት ነገሮች የሚከተሉት ናቸው፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ/ሰ/ት/ ቤቶች ማደራጃ መምሪያ 14 የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት መሠረተ ሀይማኖት ስምንተኛ ክፍል  ማመን ፦ የሰው ልጅ ከዂሉ አስቀድሞ የዓለም መድኃኒት ክርስቶስ ሕግን እንደ ሠራለት አምኖ መመለስ ያስፈልገዋል። “ለሰው ዂሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም (ወደ ሰው) የመጣው ነው፤ በዓለም ነበረ ፤ ዓለሙም በእርሱ ኾነ ፤ ዓለሙ ግን አላወቀውም። ወደ ወገኖቹ መጣ፤ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም፡፡ ለተቀበሉት ዂሉ ግን በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲኾኑ ሥልጣንን ሰጣቸው፡፡ እነርሱም ከእግዚእሔር ተወለዱ …” (ዮሐ. ፩፥፱)። ቀደም ሲል የነበረው ድኅነት ለተቀበሉትም ላልተቀበሉትም የተደረገ፤ ላመኑትም ላላመኑት የተፈጸመ ድኅነት ነው። አሁን ግን ላመኑ እንጂ ላላመኑ የሚሰጥ ድኅነት የለም፡፡  መጠመቅ ፦ ለመዳን ማመን ብቻ በቂ አይደልም። ምክንያቱም በማመን ብቻ ከተባለ አጋንንትም እምነት አላቸው። ዕለት ዕለት የሚድኑበት፣ የሚጨመሩበት መንገዱ እምነትና ጥምቀት ነው፡፡ “ያመነ የተጠመቀ ይድናል” (ማር. ፲፮፥፲፮) በማለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስላስተማረን ለመዳን እምነት ቀጥሎም መጠመቅ ያስፈልጋል። ይህን ካሣ ተፈጽሞ የተሠራውን ሕግ መፈጸም ግዴታ ሲሆን የቅዱሳን ሐዋርያት ተግባርም ይህ ነበር። ሕይወትን ድኅነትን መስበክ ፤ ያመነውን ማጥመቅ ፤ የድኅነቱ ተሳታፊ ማድረግ ወደ ድኅነቱ ማስገባት ፤ የሕይወትን ቃል ለዂሉ መመስከር ነው። ዓላማው ለማሳመን ፣ ለማጥመቅ ፣ ለማዳን ነው። ለመዳን አምኖ መጠመቅ የግድ አስፈላጊ መኾኑን በሐዋርያት ሥራ የተመዘገበው የጃንደረባው ታሪክ ያስረዳናል (ሐዋ. ፰፥፴፭-፴፯)። ማመን ብቻውን ስለማያድን ጃንደረባው ‹‹አምናለሁ›› ብሎ ከማመን አልፎ ሀይማኖቱን መስክሯል፤ ፊልጶስም ‹‹ድነኀል፤ ሒድ›› አላለውም፤ አጠመቀው እንጂ፡፡ ስለዚህ ከእምነት ቀጥሎ መጠመቅ ለድኅነት ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ነው ዓለምን ለማዳን የመጣው አምላካችን ሐዋርያትን ወደ ዓለም ዂሉ የላከው (ማቴ. ፳፰፥፲፱)፡፡ ተልዕኮውም እንዲያምኑ፣ እንዲጠመቁ፣ ትእዛዙን እንዲጠብቁ፣ ደቀ መዛሙርት እንዲኾኑ ነው፡፡ ድኅነት የሚገኘው በዚህ መንገድ ነው።  ከምሥጢረ ቁርባን መሳተፍ ፦ ሰው ካመነ ከተጠመቀ በኋላ ማድረግ ያለበት ቅዱስ ሥጋውን መብላት፣ ክቡር ደሙን መጠጣት ነው። ሥጋ ወደሙ ሕይወት የሚገኝበት የእምነት እና የጥምቀት ማተሚያ መደምደሚያ ነው። እምነት መሠረት ፤ ጥምቀት መሠረት የሚጸናበት ከእግዚአብሔር የምንወለድበት ሲሆን ሥጋው እና ደሙ ማረጋገጫ ነው። ያመነ በጥምቀት ይወለዳል ፤ የተወለደ ደግሞ የሚያድግበት ምግብ ያስፈልገዋል፤ ምግቡም ሥጋውና ደሙ ነው። ይህን በልቶ ጠጥቶ የሚኖር ሰው የእግዚአብሔር ልጅ የመንግሥቱ ወራሽ ፣ የስሙ ቀዳሽ ይኾናል። “የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ለዘለዓለም ሕይወት ለሚኖር መብል ሥሩ እንጂ ለሚጠፋው መብል አይደለም፤ ይህን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና … የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ፤ ለዓለም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና …” ተብሎ እንደ ተጻፈ (ዮሐ. ፮፥፳፯-፶፬፤ ሮሜ. ፭፥፱፤ ኤፌ. ፩፥፯፤ ፩ኛ ዮሐ. ፩፥፯)። ስለዚህ አምነን ተጠምቀን ሥርየት የተገኘበትንና የሚገኝበትን ሥጋውን መብላት ያስፈልጋል። በሀይማኖት ከብረን፣ በጥምቀት ተወልደን፣ በሥጋው በደሙ ታትመን ድኅነትን ገንዘብ እናደርጋለን።  በጎ ሥራን መሥራት ፦ መልካም ሥራ የሌለው እምነት፣ ጥምቀት፣ ቁርባን ብቻውን አያድንም፤ ያመነ የተጠመቀ ሰው ፈጣሪውን በሀይማኖት መከተል በግብር መምሰል አለበት፡፡ “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ፤” (ማቴ. ፭፥፲፮)፡፡ የሰው ልጅ ከላይ የተዘረዘሩ ተግባራትን ከፈጸመ እንደየሥራው መጠን ዋጋውን እንደሚቀበል ቅዱሳት መጽሐፍት ምስክሮች ናቸው፡፡ “እነሆ በቶሎ እመጣለሁ፤ ለእያንዳንዱ እንደየሥራው መጠን እከፍለው ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር ነው፤” (ራእ. ፳፪፥ ፲፪፤ ያዕ. ፪፥፳፮)፡፡ ከዚህ የምንረዳው አምላካችን ለፍርድ ሲመጣ የሚጠይቀው ሀይማኖት ብቻ ሳይኾን ሥራ መኾኑን መዘንጋት እንደሌለብን ነው፡፡ “… ብራብ አላበላችሁኝም፤ ብጠማ አላጠጣችሁኝም፤ ብታረዝ አላለበሳችሁኝም …” እንዳለ ጌታችን (ማቴ. ፳፭፥፴፭-፵፭)፡፡ ስለዚህ ለድኅነቱ ተግባር አስፈላጊ ነው፡፡ ከተግባር ጋር ዐቂበ ሕግ (ሕግ መጠበቅ) ተገቢ ነው፡፡ “የዘለዓለም ሕይወትን አገኝ ዘንድ ምን ላድርግ?” ብሎ ለጠየቀው ጐልማሳ ጌታችን የሰጠው ምላሽም “… ትእዛዛትን ጠብቅ” የሚል ነው (ማቴ. ፲፱፥፲፮-፲፯)። የዘለዓለም ሕይወትን ለመውረስ እግዚአብሔር በቸርነቱ የሚቀበለው መልካም ሥራ ወሳኝ ጉዳይ ነው።  በሀይማኖት በምግባር መጽናት ፦ ለመዳን ከማመን፣ ከመጠመቅ፣ ሥጋውን ከመብላት፣ ደሙን ከመጠጣት በተጨማሪ በዚሁ ጸንቶ መኖር ያስፈልጋል፡፡ ገብተው የወጡ፤ አምነው የካዱ ኹሉ ድኅነት የላቸውም። “በኹሉም ዘንድ ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትኾናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል፤” (ማቴ. ፲፥፳፪፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ/ሰ/ት/ ቤቶች ማደራጃ መምሪያ 15 የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት መሠረተ ሀይማኖት ስምንተኛ ክፍል ፳፬፥፲፫፤ ማር. ፲፫፥፲፫) ። የሰው ልጅ የሚድነው በእምነት፣ በጥምቀት፣ በሥጋው በደሙ፣ በመልካም ሥራ ጸንቶ ሲኖር ነው። ፪.፬. ወላዲተ አምላክ በነገረ ድኅነት ውስጥ ያላት ሱታፌ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት ውስጥ ያላት ድርሻ(ሱታፌ) ከቅዱሳን መላዕክት ፣ በዘመነ ብሉይ ከነበሩት ነብያት ለተለያዩ የእግዚአብሔር ሰዎች ካደረጉት ድርሻ ዘጸ ፴፪፥፴፪ ፤ ዳን ፫፥፳፰ እጅጉን የላቀ ነው። የሰው ልጅ በኃጢአቱ ምክንያት ካገኘው ውድቀት የባሕርይ መጎስቆልና በእግረ ከይሲ መረገጥ የተላቀቀው በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምክንያትነት በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አዳኝነት ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን በተለየ አካሉ የተገለጠ ቢሆንም ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ግን የተለየበት ጊዜና ሰዓት የሌለ ስለሆነና መለያየትም የሌለ በመሆኑ የሰው ልጅ ድኅነት የአምላክ የማዳን ሥራ ነው። በዚህም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለድኅነተ ዓለም እግዚአብሔር አምላክ እናት አድርጎ ከርሷ ስለተወለደ ወላዲተ አምላክ ትባላለች ። በዚህም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት ውስጥ ካላት ድርሻዎች መካከል የአምላክ እናት መሆኗ አንዱ ነው። የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት ውስጥ ያላት ሱታፌ የሚጀምረው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመውለድ በተገባ በንጽሕና በድንግልና ከመገኘት ጀምሮ ነው። “እግዚአብሔር አብ ከሰማይ ወደ ምድር ተመለከተ ፤ ሰሜንና ደቡቡን ምሥራቅና ምዕራቡን አሻተተ እንዳቺ ያለ አላገኘምና የሚወደውን አንድ ልጁን ወዳንቺ ላከ ” (አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም) እግዚአብሔር አምላክ እመቤታችንን ከመርገም ከቁራኝነት ጠብቋታል። ይህ ሲባል ግን እመቤታችን ሳትበቃና ሳትነጻ ከሌላው ሰው አድልቶ ያደረገላት ነገር ኖሮ ሳይሆን በኋላ ላይ የሚኖራትን ጽናት እና ቅድስና በአዋቂነቱ ተመልክቶ ያደረገላት መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል። ለምሳሌ ፦ ነብዩ ኤርምያስን “በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፤ በማኅጸንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፤ ለአሕዛብም ነብይ አድርጌሃለሁ” (ኤር ፩፥፲፭) በማለት ለነብይነትና ለቅድስና የመረጠው ያለጸጋውና ያለትጋቱ ሳይሆን የበኋላ ትጋቱንና ጽናቱን በአምላክነቱ ዓይቶ መምረጡን ለመናገር ነው። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ትቶ ስለ ነገረ ድኅነት ማሰብ የሚቻል አይደለም። በብሉይ ኪዳን ለሰው ልጅ ድኅነት ምልክት ኾና የተሰጠች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት ። ይህንንም “እነኾ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል።” በማለት የድንግል በድንግልና ጸንሶ በድንግልና መውለድ ለአምላክ ሰው መሆን ዋና ምልክት ኾኖ በነብየ እግዚአብሔር ተገልጾ እናገኘዋለን። ኢሳ ፯፥፲፬ ዓለምን የሚያድነው አምላክ ሰው መሆኑና በሥጋ መገለጡ በማያሻማ ሁኔታ የታወቀው ከድንግል በመወለዱ ነበር። ስለዚህ እመቤታችን ድንግል ማርያም የተወለደው ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ መድኃኒት መሆኑን በትክክል ለማወቅ ዋናዋ ምልክት ናት ። እርሷን አለመረዳት ልጇን ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲሁም በአጠቃላይ ነገረ ሥጋዌን በትክክል አለመረዳት ነው ። ከብሉይ ኪዳን ወደ ሐዲስ ኪዳን ስንሸጋገር የግድ መሐል ላይ የምናገኛት እርሷ በመሆኗ እግዚአብሔር ወልድ ሰው የሆነባትን እመቤታችንን አልፎ ነገረ ሥጋዌን ማንሣት አይቻልም። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከፍጥረታት ኹሉ የተለየ ቦታ ያላት ሲሆን ለእርሷ የተሰጣትን ልዩ ቦታ ከእርሷ በፊትም ኾነ ከእርሷ በኋላ ለማንም ያልኾነና መቼም መች ሊሆን የማይችል ነው። ምክንያቱም ከፍጥረታት ወገን ፈጣሪዋን የፀነሰችና የወለደች ከእርሷ በፊትም አልነበረም ከእርሷ በኋላም አይኖርም ። ንጽሕተ ንጹሐን ቅድስተ ቅዱሳን እመቤታችን ድንግል ማርያም እርሱ እግዚአብሔር ባወቀ ባዘጋጀው ሰውን የማዳን መለኮታዊ ዕቅድ ውስጥ ከጥንቱ ከዘለዓለሙ የታሰበችና የተዘጋጀች ምርጥ ዕቃ ነበረች። የእግዚአብሔር የማዳኑ ሥራ እንዲሁ በድንገት የሆነ በእርሱ ዘንድ ያልታሰበ ሳይሆን እኛ ልንደርስበት በማንችለው ረቂቅ መለኮታዊ ሐሳብና ዕቅድ ውስጥ የታወቀ ነው። ስለሆነም እግዚአብሔር አምላክ ሰው የሚሆንባት እና ለምክንያተ ድኅነት የመረጣት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አስቀድማ በአምላክ ኅሊና በሰው ልጅ የድኅነት ሱታፌ ውስጥ ተካታ ታስባለች ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ/ሰ/ት/ ቤቶች ማደራጃ መምሪያ 16 የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት መሠረተ ሀይማኖት ስምንተኛ ክፍል የምዕራፍ ፪ ማጠቃለያ ጥያቄዎች፤ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ትክክል ከሆኑ እውነት ስህተት ከሆኑ ደግሞ ሐሰት በማለት መልስ ስጡ፡፡ ፩ በነገረ ድኅነት አስተምህሮ መሠረት የሰውን ልጅ ከውድቀቱ ክሞቱ የታደጉት ቅዱሳን መላዕክት ናቸው ። ፪ በነገረ ድኅነት አስተምህሮ መሠረት የሰው ልጅ የዳነው ከኃጢአት ፍዳ ብቻ ነው ። ፫ ስለ ሰው ልጅ ድኅነት ያለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ማሰብ አይቻልም ። ለሚከተሉትን ጥያቄዎች ትክክለኛውን መልስ ስጡ ። ፬ ነቢያት ፣ መላዕክት እና የኦሪት መስዋዕት የሰውን ልጅ ስለምን ማዳን አልተቻላቸውም ? ፭ በነገረ ድኅነት አስተምህሮ መሠረት የሰው ልጅ ወደቀ ስንል ምን ማለታችን ነው ? ፮ ሰው የዳነው ከምንድነው ? በዝርዝር በመግለጽ አብራሩ ። ፯ የሰው ልጅ በነገረ ድኅነት ውስጥ ማድረግ የሚገቡት ምንምን ነገሮች አሉ ? አብራሩ። ፰ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት ውስጥ ያላት ሱታፌ ምንድነው ? በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ/ሰ/ት/ ቤቶች ማደራጃ መምሪያ 17 የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት መሠረተ ሀይማኖት ስምንተኛ ክፍል ምዕራፍ ሦስት ዓላማ ተማሪዎች ይህንን ትምህርት ተምረው ሲያጠናቅቁ ፩. በነገረ ድኅነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች የቤተክርስቲያን አስተምህሮ እና ምላሽ ምን እንደሆነ ያውቃሉ ይረዳሉ። የመክፈቻ ጥያቄ ፩. በቤተክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት ድኅነት በቅጽበት የሚደረግ ነውን ? ፫. በነገረ ድኅነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች እና መልሶቻቸው ፫.፩. ድኅነት በጸጋ ብቻ ነውን ? የሰው ልጆች ሁሉ ድኅነት የእግዚአብሔር የጸጋው ሥጦታ ነው ። ያድነን ዘንድ አስቀድሞ የወደደና የፈቀደ ይህን አባታዊ ፍቅሩን ለመፈጸም ሰው የሆነ መከራን የተቀበለና በመከራው ያዳነን እርሱ እግዚአብሔር ነው። መዳን የእግዚአብሔር የጸጋው ሥጦታ ነው የሚባለው የሰው ልጅ በሠራው ወይንም የተገባው ሆኖ ሳይሆን ፍጹም የሆነው የእግዚአብሔር ሥጦታው ስለሆነ ነው። ሆኖም ግን እግዚአብሔር እኛን ለማዳን የእኛን ፈቃደኝነት የማይፈልግ እና በራሱ ውሳኔ ብቻ የሚፈጽም አምላክ አለመሆኑን መረዳት አስፈላጊ ነው። የሰው ነጻ ፈቃዱ የተሰጠው ከእግዚአብሔር ስለሆነ ሰው ራሱ እግዚአብሔር ያዘጋጀውን የመዳን ጸጋ የራሱን የእግዚአብሔርን የማዳን ጥሪ ሰምቶ እግዚአብሔር በሰጠው በዚህ ጸጋ ተጠቅሞ በፈቃዱና በምርጫው ቢቀበል መዳን የሰው ሥራ ውጤት ነው አያሰኘውም ወይም ጸጋነቱን አያስቀረውም ። ከዚህ በበለጠ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ፈታሒነት የሚያዋሕድ ድንቅ የእግዚአብሔር አሠራር ሆኗል። “ ሁሉ ካንተ ዘንድ ነውና ፤ ከእጅህም የተቀበልነውን ሰጥተንሃልና ” “ አቤቱ አምላካችን ሆይ ለቅዱስ ስምህ ቤት እንሠራ ዘንድ ይህ ያዘጋጀነው ባለጠግነት ሁሉ ከእጅህ የመጣ ነው።” ፩ ዜና ፳፱፥፲፬ ስለዚህ እርሱ የሰጠንን ነጻ ፈቃዳችንን መልሰን ለእርሱ ብንሰጠው ይህ መዳንን የእኛ ሥራ ነው የሚያሰኝ አንዳችም ነገር የለውም ። ስለዚህ የሰው ልጅ ድኅነት ያለ ሰው ልጅ ፈቃድ የሆነ በእግዚአብሔር ቅድመ ውሳኔ ላይ ያለቀ ነገር አይደለም ። እግዚአብሔር የሚያምኑትንና የማያምኑትን ጥንቱን አስቀድሞ ያውቃቸዋል። ይህ ማለት ግን እግዚአብሔር የሚያምኑት እንዲያምኑ የማያምኑት እንዳያምኑ አድርጎ ወስኖባቸዋል ማለት ግን አይደለም ። አንድን ነገር አስቀድሞ እንደሚሆን ማወቅ ቀድሞ መወሰን ወይንም መንሥኤ መሆን ማለት አይደልም። ጸጋ ብቻ የሚለው ኀሳብ የሰውን ልጅ ነጻ ፈቃድ የሚነሣ ነው። ይህ ማለት ለድኅነት ጸጋ ብቻ ከተባለ የሰው ልጅ የተወሰነበትን ከመቀበል ውጪ የመምረጥና የመቀበል ሆነ ያለመቀበል መብት የለውም። እያንዳንዱ ሰው በራሱ ነጻ መዳን ላይ መዳንን መሻትና ወድዶና ፈቅዶ የመቀበል ሥልጣን እዳይኖረው ያደርገዋል። ይህ ከቅዱስ መጽሐፍ አስተምህሮ መሠርት ትክክል አይደልም ። ጌታችን መሠረታዊ የሆነውን የወንጌል ትምህርት ካስተማረ በኋላ ሲያጠቃልል “ ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል።... ይህንም ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል። ዝናቡም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት መታው ወደቀም አወዳደቁም ታላቅ ሆነ። ” ማቴ ፯,፥፳፬–፳፯ በማለት አስተምሯል ።በዚህ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ውስጥ የምንረዳው የሰው ልጅ በተሰጠው ነጻ ፈቃድ ተጠቅሞ ቃሉን ማድረግም ሆነ አለማድረግ የሚችል መሆኑን ነገር ግን ቃሉን ሰምቶ የማያደርገው አወዳደቁ ከባድ እንደሆነ ነው። ሐዋርያትም ቃለ እግዚአብሔርን መሠረት አድርገው አስተምረዋል “ እነሆ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆም የመዳን ቀን አሁን ነው።” በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ/ሰ/ት/ ቤቶች ማደራጃ መምሪያ 18 የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት መሠረተ ሀይማኖት ስምንተኛ ክፍል ፪ቆሮ ፮፥፩–፪ በማለት መዳን የሚገኝበት ሰዓት ሰምተን የምናምንባትና መዳንን ገንዘብ ለማድረግ የሚያስፈልገውን ነገር ለማድረግ የምንጀምርበት ጊዜ መሆኑን አስረድቶናል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን ያውቁና ያምኑ ዘንድ ከጥንት ጀምሮ በነቢያት ትንቢት በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ስብከት እንዲሁም እርሱ ራሱ በቃልና በተአምራት ብዙ መልካም ነገር ቢያደርግላቸውም በተደረገላቸው እና በተሰጣቸው ጸጋ መጠቀም ያልቻሉትን አይሁድ “ ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርሷ የተላኩትንም የምትወግር ዶሮ ጫጩቶቿ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ አልወደዳችሁምም ። እነሆ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል። ” ማቴ ፳፫፥፴፯–፴፰ ብሏቸዋል ። የእግዚአብሔር ፈቃድ እነርሱን መሰብሰብ ሲሆን እነርሱ ግን ይህን አለመፈለጋቸውን ከዚህም የተነሣ ቤታቸው የተፈታ ሆኖ የሚቀር መሆኑ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሳይሆን የአይሁድ የራሳቸው ምርጫና ውሳኔ ውጤት መሆኑን በግልጽ ተናግራል። ሰው በእግዚአብሔር ማመኑና ወደ እርሱም መቅረቡም ሆነ አለማመኑና አለመቅረቡ በራሱ በሰውየው የሚወሰን እንጂ እንዲመጡ የሚያደርጋቸውን ሰዎችም ሆነ እንዳይመጡ የሚያደርጋቸውን ሰዎች ያለ እነርሱ ፈቃድ ራሱ እግዚአብሔር አስቀድሞ የወሰነባቸው አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። በሰሊሆም መጠመቂያ ለሠላሳ ስምንት ዓመት በደዌ የነበረው ሰው ከፈወሰው በኋላ በመቅደስ አግኝቶት “ እነሆ ድነኀል ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ ” ዮሐ ፭፥፲፬ ያለው የቀድሞው መጻጉ ከደረሰበት የባሰ እንዳይደርስበት ለማድረግ እርሱ የራሱ የሆነ ሐላፊነትና ድርሻ እንዳለው ለመግለጽ ነው። ስለዚህ ከዚህ የምረዳው የሰው ልጅ የሚድነው በጸጋ ብቻ ሳይሆን በተሰጠው ጸጋ ተጠቅሞ በማመንና በመሥራት ማለትም በተሰጠው ነጻ ፈቃድ መልካሙን በመምረጥ መትጋት ሲችል ነው። ፫.፪. ድኅነት በእምነት ብቻ ነውን ? የነገረ ድኅነትን ምንነት ከላይ በዝርዝር ተመልክተናል። ሆኖም አንዳንድ መናፍቃን ድኅነት የሚገኘው በእምነት ብቻ ነው በሚል የክህደት አስተምህሮ ውስጥ ወድቀው እናገኛቸዋለን። ለዚህም የክህደት አስተምሯቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በተሳሳተ መልኩ በመተርጎም ሲናገሩ ይስተዋል ። በመሆኑም በዚህ ርዕስ ውስጥ ድኅነት በእምነት ብቻ ነው ብለው ለሚያነሱት የክህደት አስተምህሮ ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ አንጻር የምንመለከት ይሆናል። “አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት፤” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ጠቅሰው ጽድቅ የሚገኘው በእምነት ብቻ ነው በማለት ለመተርጎም ይሞክራሉ። ነገር ግን ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ድኅነት ወይንም ጽድቅ በእምነት ብቻ የሚል ትርጉምን የያዘ አይደለም። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የሚያስረዳን የጽድቅ ሥራ መነሻውና መድረሻው እምነት መሆኑን የሚያስረዳ ነው። “ ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም ፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና ነው።” ዕብ ፲፩፥፮ የምጸድቀው በእምነት ነው ስንል እምነት ማመንና መታመንን ፣ መቀበልና መተግበርን የሚያሳይ ቃል መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ያመነውን ካልፈጸምነው እምነታችን ከንቱ ነው። ለምሳሌ ፦ ሰው ውኃ ጥምን እንደሚያረካ አምኖ ውኃውን ሳይጠጣ ከጥሙ መርካት አይችልም ፤ እህል መመገብ ኃይል እንደሚሰጥ አምኖ እህልን ሳይመገብ ኃይልን ማግኘት አይችልም ፤ ልብስ ከብርድ ይከላከላልብሎ አምኖ ሳይለብስ ሙቀትን ማግኘት አይችልም ። እንደዚሁ ሁሉ እምነት ለምግባር መነሻ መሠረት እንጂ ብቻውን የሚጠቅም ነገር አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ስለ እምነት ብቻ ያስተማረ ሳይሆን ማመንን ከመታመን ጋአስተባብሮ ስለመያዝ ነው ያስተማረው። ስለጥምቀት ሲያስተምር “ ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያላመነ ግን ይፈረድበታል። ” ማር ፲፮፥፲፮ በማለት እምነትን ከምግባር አስተባብሮ መያዝ እንደሚገባ አስተምሯል። እንደዚሁም ሁሉ አምነው ተግባራዊ ምላሽ መስጠት የተገባ ስለመሆኑ ሲናገር “ ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ ” ዮሐ ፲፬፥፲፭ ፤ “ እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ” ማቴ ፲፮፥፳፬ በማለት አስተምሯል። ትእዛዛትን መፈጸምና መስቀል መሸከም ላመኑት አምላክ የሚሰጥ ተግባራዊ ምላሾች ናቸው። በዳግም ምጽዓቱ ጌታችን ለጻድቃን ሲፈርድላቸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ/ሰ/ት/ ቤቶች ማደራጃ መምሪያ 19 የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት መሠረተ ሀይማኖት ስምንተኛ ክፍል በኃጥአን ሲፈርድባቸው የሚያነሣቸው ነገሮች ስላመኑና ስላላመኑ ብቻ ሳይሆን አምነው ምግባርን ስለሠሩና ስላልሠሩ ሁሉ ነው እንጂ ። ማቴ ፳፭፥፵፪–፵፫ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የአብርሃምን ነገር ሲናገር አብርሃም አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት ያለው ስለምንድው ቢባል ጽድቅ ማለት ለእግዚአብሔር መታዘዝ እንደመሆኑ መጠን አብርሃም አምኖ ጸደቀ የተባለው ለእግዚአብሔር በመታዘዙ ነው። “ከካራን ውጣ ወደ ከነዓን ሒድ ” ሲባል እሺ ፣ “ ወንድ ልጆችህን ግረዝ “ ሲባል እሺ ፣ ዘርህ እንደ ሰማይ ከዋክብት ይበዛልሃል በዘርህም ምድር ትባረካለች ተብሎ ትልቅ ቃል ኪዳን የተገባለትን አንድ ልጁን እንዲሠዋ ከእግዚአብሔር ዘንድ ትእዛዝ ሲመጣለት ሳያወላውል እሺ በማለት ለእግዚአብሔር በመታዘዙ ምክንያት መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል። ስለዚህ አብርሃም አምኖ በተግባርም በመታመኑ እንጂ ስላመነ ብቻ የጸደቀ አለመሆኑን መረዳት ይገባል። ስለዚህ ድኅነት በእምነት ብቻ ሳይሆን አምኖ ሥራን በመሥራት ነው። ፫.፫. ሕግን ሳይጠብቁ መጽደቅ / መዳን / ይቻላል ? ሕግ የሚሠራው የሰው ልጅ ለእግዚአብሔር ያለው ፍቅር እንዲገልጽ ነው። የሰው ልጅን እግዚአብሔር ከፈጠረው በኋላ ለእግዚአብሔር ያለውን ፍቅርና ታዛዥነት እንዲሁም ታማኝነት እንዲገልጽበት የሰጠውና ቢጠብቀው ዘለዓለማዊ መንግሥቱን እንደሚወርስ የተሰጠውን ሕግ ደግሞ ባይጠብቀው የሞት ሞት እንደሚሞት ቃል ኪዳን የገባለት ለዚሁ ነው። ነብዩ ሕዝቅኤል ይህንን ?

Use Quizgecko on...
Browser
Browser